ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ ጦርነቱን ለመቋጨት ላቀረበችው መነሻ ሐሳብ በኢራን የተሰጠው ምላሽ ተቀባይነት የለውም – ዶናልድ ትራምፕ

By Adimasu Aragawu

May 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በኢራን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለመቋጭት ላቀረበችው መነሻ ሐሳብ በኢራን በኩል የተሰጠው ምላሽ ፍጹም ተቀባይነት የለውም አሉ፡፡

ሁለቱን ሀገራት በምታሸማግለው ፓኪስታን በኩል ኢራን ምላሿን ልካለች።

በዚህም በሁሉም ግንባሮች ያለውን ጦርነት በአስቸኳይ ማቆም፣ አሜሪካ የኢራን የባሕር እንቅስቃሴ መገደቧን እንድታቆም፣ በኢራን ላይ የተጣሉ ሁሉም አይነት ማዕቀቦች እንዲነሱ እና ከዚህ በኋላ ሀገሪቱ ላይ ምንም አይነት ጥቃት እንደማይኖር ዋስትና ማግኘትን ጠይቃለች፡፡

በተጨማሪም ኢራን ጦርነቱን በዘላቂነት ለማቆም ለወደሙባት መሰረተ ልማቶች የካሳ ክፍያ እንዲሁም በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ያላት ሉዓላዊ አስተዳደር እንዲከበርላት መፈለጓን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦርነቱ በቅርቡ ያበቃል ቢሉም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው÷ ጦርነቱን ለመቋጨት ኢራን የምታበለጽገውን የዩራኒየም ንጥረ ነገር ሙሉ ለሙሉ ማቆሟን ከግንዝቤ ማስገባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢራን ዩራኒየምን የምታበለጽግባቸው ማዕከላት አሁንም እንዳሏት አመልክተዋል፡፡

ለአሜሪካ ያቀረቡትን ቅድመ ሁኔታ በይፋ ያልተናገሩት የኢራኑ ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን በበኩላቸው÷ በጠላቶቻችን ፊት አንገታችንን አንደፋም፤ እየተደራደርን የምንገኘውም ስለተሸነፍን አይደለም ብለዋል።

በፓኪስታን በኩል ከኢራን የደረሳቸውን ጦርነት የማቆም መነሻ ሐሳብ ማንባባቸውን በማህበራዊ ሚዲያቸው የገለጹት ዶናልድ ትራምፕ÷ ሐሳቡን አልወደድኩትም፤ ፍጹም ተቀባይነት የለውም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በአቤል ነዋይ