አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ደቡብ ኮሪያ ከሳምንታት በፊት በሆርሙዝ ሰርጥ ውስጥ በጭነት መርከቧ ላይ ለተፈፀመው ጥቃት አፀፋ እመልሳለሁ ስትል ዛተች፡፡
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በመርከቧ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በጽኑ አውግዟል፡፡
ናሙ የተሰኘችዋ መርከብ ምንም አይነት ህግ እንዳልጣሰች የገለጸው የኮሪያ መንግሥት፤ ድርጊቱ በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም የተደነገገውን ዓለም አቀፍ የባህር ሀይል ሕግ የጣሰ መሆኑን አመልክቷል።
ጥቃቱ በየትኛው አካል እንደተሰነዘረ እየተጣራ እንደሆነ የገለጸችው ደቡብ ኮሪያ÷ የጥቃቱ ምንጭ እንደታወቀ የአፀፋ መልስ እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡
ጥቃቱን በተመለከተ የደቡብ ኮሪያ ባለሙያዎች የመጀመሪያ ደረጃ የፎረንሲክ ትንታኔ ማድረጋቸውን ሚያሚ ሄራልድ ዘግቧል፡፡
አንዳንድ ምንጮች በጥቃቱ ኢራንን ቢወነጅሉም በደቡብ ኮሪያ የኢራን ኤምባሲ ውንጀላውን ውድቅ አድርጎታል።
ጥቃቱን ለማጣራት በሚደረገው ጥረት ኢራን አስፈላጊውን ትብብር እንደምታደርግም አረጋግጧል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው÷ ከኢራን የተተኮሱ ሚሳኤሎች የደቡብ ኮሪያን መርከብ መምታታቸውን በመግለፅ አሜሪካ የሆርሙዝ ሰርጥን ለማስከፈት የምታደርገውን ጥረት ደቡብ ኮሪያ እንድታግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ