አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ፎርዋርድ ጉባኤ በአፍሪካ አህጉር እና በፈረንሳይ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የአፍሪካ ፎርዋርድ 2026 ጉባኤን የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡
ጉባኤው በአፍሪካ እና በፈረንሳይ መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ ለመጀመር ያለመ ነው፡፡
ጉባኤው የሀገራት መሪዎችን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ ባለሀብቶችን፣ ሥራ ፈጣሪዎችን እና የልማት አጋሮችን በማሰባሰብ በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡
ጉባኤው ቀጣይነት ያለው የኢነርጂ ሽግግር፣ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የምግብ ዋስትና፣ የጤና፣ ዘላቂ የግብርና ልማት፣ መሰረተ ልማት፣ ፈጠራ እና ዕድገት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፡፡
አፍሪካ ፎርዋርድ ጉባኤ አጋርነትን ለማጠናከር፣ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ እድገትን ለመደገፍ ያለመ ሲሆን ከኢኮኖሚ ልማት እስከ ዓለም አቀፋዊ አስተዳደር ድረስ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ተጨባጭ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል፡፡
በጉባኤው የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት እና የኃይል ሽግግርን በተመለከተ የኢትዮጵያን ተሞክሮ አካፍለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሁለቱ ዘርፎች የጀመረችውን ስራ በማጠናከር የላቀ ሚና መጫወቷን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
ፈረንሳይ በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ባለሃብቶችም በፈረንሳይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ፍላጎት እንዳላት የገለጹት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ሀገራት ተግባራዊ የሚሆን የ23 ቢሊየን ዩሮ የኢንቨስትመንት ጥቅል ይፋ አድርገዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ጥቅሉ በኢነርጂ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በባህርና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በግብርና ዘርፎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡