የሀገር ውስጥ ዜና

ውስጣዊ አቅማችን ለዓለም አቀፍ አጋሮችና ወዳጆች ትልቅ መተማመንን ፈጥሯል – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

By Adimasu Aragawu

May 13, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ውስጣዊ አቅማችን ዲፕሎማሲያዊ ከፍታችንን በማላቅ ለዓለም አቀፍ አጋሮችና ወዳጆች ትልቅ መተማመንን ፈጥሯል አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።

አገልግሎቱ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

ውስጣዊ አቅማችን ዲፕሎማሲያዊ ከፍታችንን በማላቅ ለዓለም አቀፍ አጋሮችና ወዳጆች ትልቅ መተማመንን ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች የሀገራዊ ሉዓላዊነት እና የቀጠናዊ መሪነት ማረጋገጫ ሆነዋል። በተለይም ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር ረገድ ታሪካዊ የተባሉ የዲፕሎማሲ ድሎችን እያስመዘገበች ትገኛለች። ውስጣዊ አቅምን በማጎልበትና አጋርን በማብዛት ላይ የተመሰረተው ስትራቴጂካዊ አካሄድ፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት በማሳደግ በጂኦ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ወሳኝ ተዋናይ እንድትሆን አስችሏታል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ የተጽኖችን አድማስ ከፍታን ያበሰረ ውስጣዊ አቅማችን የፈጠረው የዲፕሎማሲ ድላችን ነው፣ ብሪክስ ኢትዮጵያ በታዳጊ ሀገራት መካከል ያላትን ስልታዊ ሚዛን በመጠበቅ፣ የፋይናንስ ምንጮቿን በማስፋትና በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪነት ላይ ያላትን ድምፅ በማጠናከሯ የተገኘ ውጤት ነው። በተለይም ታላላቅ የዓለም ኃያላን ሀገራት ኢትዮጵያን እንደ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ አጋር የመምረጥ አዝማሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ፣ የመንግሥትን ዲፕሎማሲያዊ ብስለትና ሀገሪቱ ያላት የማይተካ ጂኦ-ፖለቲካዊ ክብደት እየገዘፈ መምጣቱን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

መንግሥት የህዳሴ ግድብን (GERD) በተመለከተ ያሳየው ጽናት እና ብልህ የድርድር አቅም የኢትትዮጵያን የዲፕሎማሲ ጉዞ ወደላቀ ምዕራፍ ያሸጋገረ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን የተፈጥሮ መብት በተግባር አረጋግጧል።

ምንም እንኳ የተለያዩ የውጭ ጫናዎች ቢበዙም፣ መንግሥት “የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፍትሄ” በሚል መርህ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥ መቻሉ እና ህዳሴዋን በስኬት ማጠናቀቁ የዲፕሎማሲው ጥንካሬ ዋነኛ ማሳያ ሆኗል። ይህ የሉዓላዊነት ድል ሀገሪቱ በራሷ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመምራትና የመጨረስ ብቃቷን ለዓለም የመሰከረችበት ታላቅ ክስተት ነው።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ለሚታዩ ግጭቶች መፍትሄ በመፈለግ እና ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን በመምራት መቻሏ የቀጠናው የሰላም እና የጸጥታ ምሰሶ መሆኗን ዳግም አረጋግጧል። በተለይም በኤሌክትሪክ ኃይል እና በመሠረተ ልማት ጎረቤት ሀገራትን የማስተሳሰር ስራው “የጋራ እድገት” መርህን በተግባር ያሳየ ሲሆን፣ ይህም ለቀጠናው ሰላም እና የተረጋጋ ፖለቲካዊ መስተጋብር እንደ መሠረት ተወስዷል።

በሌላ በኩል፣ መንግሥት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል የባህር በር ማግኘት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፣ ይህንኑ ፍላጎት በሰላማዊ መንገድ እና “በመስጠት እና በመቀበል” መርህ ለማሳካት የጀመረው እንቅስቃሴ ደፋር እና ስልታዊ እርምጃ ነው። ይህ ጉዳይ ለዓመታት ታፍኖ የቆየ ሀገራዊ አጀንዳን ወደ አደባባይ በማውጣት፣ ቀጠናዊ ትብብርን በሚያጠናክር መልኩ እንዲፈታ መንግሥት የወሰደው ተነሳሽነት የቀጣይ ትውልድን እድል የሚወስን የፖሊሲ ብስለት ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም ዘመናዊ የዲጂታል ዲፕሎማሲ መድረኮችን በመጠቀም የሀሰተኛ መረጃዎችን በመመከት እና የሀገር ውስጥ የልማት ስኬቶችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ በማድረግ የኢትዮጵያን ገጽታ መልሶ የመገንባት ስራ ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ይገኛል ።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እየተከተለው ያለው የዲፕሎማሲ አቅጣጫ “ጠንካራ ኢትዮጵያ ለበለፀገ ቀጠና” የሚል ግልጽ ራዕይ ያለው ነው። ታላላቅ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የፈቀዱት፣ መንግሥት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን በብቃት በመቋቋም ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ብቃቱ ለዓለም አቀፍ አጋሮች ትልቅ መተማመንን በመፍጠሩ ነው።

ሀገራችን በውስጣዊ ሪፎርሞች እያከናወነች ያለችው የልማት ስራ ከዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬዋ ጋር ተዳምሮ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ተሰሚ ፣ በዓለም አቀፍ መድረክም የማትታለፍ ኃይል መሆኗን አስመስክሯል። ኢትዮጵያ ዛሬም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሉዓላዊነት እና የጥንካሬ ተምሳሌት በመሆን ጎዞዋን አጠናክራለች።