አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዲጂታል አሰራርን ወደ ተግባር ለማስገባት የተከናወነው ስራ የምርጫ ሂደቱን ታማኝነት የበለጠ የሚያረጋግጥ ነው አሉ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን።
የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የዴሞክራሲ ተቋማትን ከመገንባትና ብቁ የሆኑ አመራሮችን በገለልተኝነት ከመመደብ አንጻር ከፍተኛ መሻሻሎች ታይተዋል።
6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካከናወነቻቸው ምርጫዎች በተሻለ መልኩ መካሄዱን አስታውሰው÷ ይህም ተቋማት የገዢው ፓርቲ መገልገያ ከነበሩበት አሰራር ወጥተው ወደ ገለልተኝነት የተሸጋገሩበትን ሂደት ያሳያል ብለዋል።
በመንግሥት በኩል የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የተለዩ ድምጾች በፓርላማ እንዲሰሙ ለማድረግ እንዲሁም ለብዝኃ ሐሳብ መከበር ቁርጠኝነት መኖሩ የሚበረታታ እንደሆነም አመልክተዋል።
የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ጌታሁን አበራ በበኩላቸው÷ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዲጂታል አሰራርን ወደ ተግባር ለማስገባት የተከናወነው ስራ የምርጫ ሂደቱን ታማኝነት የበለጠ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ዲጂታላይዜሽን የምርጫ መጭበርበርንና የታማኝነት ጉድለትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ገልጸው÷ ይህም ለዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር መሰረት ነው ብለዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ሐሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበት ዕድል መፈጠሩ ለሰላማዊ ምርጫ ወሳኝ መሆኑን አንስተው÷ ዜጎች እስከ ውጤት መግለጫ ቀን በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ተቋማትና የፍትህ ስርዓት ግንባታ ሂደት ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት ምሁራን÷ በተለይም ተቋማዊ ስርዓት እየተገነባ እና እየተጠናከረ መምጣቱ ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ኃይል እንደሚሆን አመልክተዋል።
በዮናስ ጌትነት