አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ-ፈረንሳይ ትስስር ይበልጥ እየጠነከረ ብቻ ይዘልቃል አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
የአገልግሎቱ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከ125 ዓመታት በላይ ያስቆጠረና በጠንካራ የታሪክ መሰረት ላይ ተገንብቶ ይበልጥ እየጎለበተ መጥቷል፡፡
ይህ ታሪካዊ ወዳጅነት፤ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ለዉጥ ወዲህ በእጅጉ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ወደ ልዩ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አሳድገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጥቅምት 2011 ዓ.ም. በፈረንሳይ ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት ተከትሎ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአምስት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል፡፡
ፕሬዚዳንት ማክሮን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ታሪካዊውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የጎበኙ ሲሆን፣ በዚህም ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና ለኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት እድሳት ታሪካዊ ወሳኝ ድጋፍ በማድረግ ዉጤታማ ሥራ ሰርታለች፡፡
ዛሬ ላይ የሁለቱ ሀገራት ሁለገብ ትብብር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመሠረተ ልማት፣ በሲቪል አቪዬሽን፣ በባህልና በሳይንስ ዘርፎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጎለበተ መጥቷል፡፡ በቅርቡም በመስከረም 2017 ዓ.ም. በሁለቱ ሀገራት የፓርላማ የወዳጅነት ቡድኖች መካከል የተደረገው ውይይት የፓርላማ ዲፕሎማሲን በማጠናከር ልምድ የተወሰደበት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትስስር ከ2.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡ ኩባንያዎቹ በታዳሽ ኃይልና በአቪዬሽን ዘርፎች ትልቅ ፍላጎት እያሳዩ ይገኛሉ፡፡
የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ (AFD) በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ሲሆን፣ ከ60 በላይ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተዋል፡፡
በትምህርትና ባህል ትስስርም የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፣ አንጋፋው ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት የሁለቱ ሀገራት የትምህርትና የቋንቋ ትስስር ህያው ተምሳሌት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ፈረንሳይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢነትን አጽኖት ከሰጡ ሀገራት አንዷ ስትሆን ሂደቱ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ ያላትን አቋም እና ድጋፍ ያሳየች ጠንካራ አጋራችን ናት፡፡የኢትዮ-ፈረንሳይ ትስስር ይበልጥ እየጠነከረ ብቻ ይዘልቃል!