አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተራማጅ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚከተሉ ዘመናዊ መሪ ናቸው፡፡
በፈጣኑ እና ተለዋዋጩ የዓለም ፖለቲካ ውስጥ የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር ከአውሮፓ አህጉራዊ ፍላጎትና ጥቅም ጋር በማስተሳሰር የመሪነት ሚናቸውን እየተወጡ ያሉ ብልህ ፕሬዚዳንት ስለመሆናቸው ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡
ይህ አስተሳሰባቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር ፍልስፍና ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሀገራቸውን አንድነት፣ ብሔራዊ ክብር እና ጥቅም ከአፍሪካ ሀገራት የጋራ ብልፅግና ጋር በማሰናሰል ለጋራ እድገት የሚሰሩ ፓን አፍሪካኒስት መሪ ናቸው፡፡
የፕሬዚዳንት ማክሮን የዲፕሎማሲ መርህ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገቢር ነበብ (ፕራግማቲክ)፣ በጋራ ጥቅምና መከባበር ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ አንዱን አሳንሶ ሌላውን ከፍ ሳያደርግ ሁሉንም በእኩል ዓይን ይመለከታል።
በዚህ የተነሳ የዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ከባለ አንድ ዋልታ ወደ ባለ ብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት ለመቀየር እየታገለ ባለበት በዚህ ዘመን፣ የሀገራቸውን ጥቅም ከወዳጅ ሀገራት ጋር በትብብር ለማስጠበቅ የሚተጉ መሪ ናቸው፡፡
ለየጉዳዩ እንደ ጉዳዩ መፍትሄ የሚሰጡ እንጂ፣ ለየሀገሩ የእኛን አስተሳሰብ ካልተከተላችሁ በሚል ፖለቲካዊ እሳቤዎች በርዕዮተ ዓለም ብቻ ካልተፈቱ የሚሉ መሪ አይደሉም፡፡
ገቢር ነበብ በሆነ አስተሳሰባቸውም በሀገራቸው እና በዓለም አቀፍ የፖለቲካ አውድ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ የቻሉ ፕሬዚዳንት ያደርጋቸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ማክሮን ወደ ፖለቲካው የገቡት በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ የፈረንሳይ ሶሻሊስት ፓርቲን በመቀላቀል ነው።
የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ሆላንዴ ከፍተኛ አማካሪ እና በኋላም የኢኮኖሚ፣ ኢንዱስትሪ እና ዲጂታል ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
የፕሬዚዳንት ማክሮን የፖለቲካ አቋም ፕራግማቲክ በመሆኑ የቆየውን የፈረንሳይ ሶሻሊስት የፖለቲካ ባህል መቀየር እንዳለባቸው ያስባሉ፡፡
አስበውም አልቀሩም በፈረንጆቹ 2016 ማክሮን የራሳቸውን የፖለቲካ እንቅስቃሴው “ኤን ማርሼ” ን መሰረቱ፡፡
በተራማጅ አስተሳሰባቸው የሚታወቁት ፕሬዚዳንቱ፤ ለሀገራቸው ፈረንሳይ እና ለአህጉራቸው አውሮፓ አንድነት ያላቸው ፅኑ እምነት የዘመኑ ፓንአውሮፓዊ ያደርጋቸዋል፡፡
ይህ አስተሳሰባቸው ከሀገራቸው እና ከአውሮፓ ወዳጅ ሀገራት ድጋፍን አስገኝቶላቸዋል።
ማክሮን ሀገራቸውን በተለያዩ የሥራ መስኮች፣ በዲፕሎማሲ እና በሚኒስትርነት ሲያገለግሉ ቆይተው፤ ግንቦት በፈረንጆቹ 2017 የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ የፖለቲካ አስተሳሰባቸው ተፈላጊ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪና ተመራጭ እንዳደረጋቸው አስመሰከረ፡፡
በመጀመሪያ ዙር ከ2017 እስከ 2022 በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት ማክሮን፤ እሳቤያቸው እና ድርጊታቸው መልካም በመሆኑ ምናለ ቢደግሙ በሚል ለሁለተኛው ዙር የፕሬዚዳንትነት ሚናቸው ከ2022 ጀምሮ እስከ አሁን ማለት ነው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ የሀገራቸው ህዝብ እድል ሰጣቸው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ሲመጡ፡-
👉 የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን አደረጉ፡- የተንዛዛ የገበያ ሰንሰለትን በመቀየር፣ በስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕሩነርሺፕ ላይ በማተኮር የፈረንሳይን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ተግተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት የጋራ ልማት እና የተጠቃሚነት ፖሊሲን በይፋ ያራመዱ አውሮፓዊ መሪ አድርጓቸዋል፡፡
👉 የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎች፡- የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት እና የካርበን ልቀትን ለመቀነስ እርምጃዎችን ጨምሮ ትልቅ የአካባቢ ጥበቃ አጀንዳዎችን አራምደዋል። በአረንጓዴ ዐሻራና በዓለም መድረክ ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካቶች ለሚታገሉለት ዓላማ የተሰለፉ ግንባር ቀደም መሪ ያደርጋቸዋል፡፡
👉 የአውሮፓ ውህደት/ፓንአውሮፓዊነት፡- ማክሮን የዩሮ ዞንን ማጠናከር እና የበለጠ የተዋሃደ የአውሮፓ ህብረት መፍጠርን ጨምሮ ጥልቅ የአውሮፓ ውህደት እንዲፈጠር ጠንካራ ጠበቃ ናቸው። በዚህም በሀገራቸው እና በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት አድናቆትን አትርፈዋል።
👉 ማህበራዊ ጉዳዮች፡ -ማክሮን እንደ የፆታ እኩልነት ያሉ ማህበራዊ ጉዳዮችን ፈትተዋል፤ የትምህርት እና የጤና ተደራሽነትም እንዲሰፋ ማሻሻያ ተግብረው ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡
👉 የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፡- በዓለም አቀፍ መድረክ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ እና በአፍሪካ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት እንዲሁም በአውሮፓ ህብረት ውስጥ የፍራንኮ-ጀርመን ግንኙነትን ለማጠናከር ሲሰሩ ቆይተዋል።
ፕሬዚዳንት ማክሮንን ብዙዎች በፖለቲካ እሳቤያቸው ተራማጅ ይሏቸዋል፡፡
በተለዋዋጭ ዓለም፣ ፈጠራ፣ ፍጥነትን እና ፕራግማቲክ ዘይቤን በመጠቀም የሀገራቸውን አንድነት፣ ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ፣ ሀገራቸው በዓለም መድረክ ያላትን ክብር ለመጠበቅ በትብብር የሚሰሩ አስብሏቸዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙ ወቅታዊ እና ውስብስብ ፈተናዎችን በጥበብ በመምራትና በማለፍ ይታወቃሉ፡፡
በፈረንሳይ እና በአውሮፓ ፖለቲካ ማክሮን ዋነኛው የለውጥ አራማጅ ሰው ናቸው።
የማክሮን የአመራር ጥበብ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ የፈረንሳይ እና የአውሮፓን የፖለቲካ ፍልስፍና አቅጣጫ በመቅረጽ የዘመኑ ታዋቂ እና ተደማጭነት ያላቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪ አድርጓቸዋል፡፡