ስፓርት

በፒኤስጂ ስኬታማ ዓመታት እያሳለፈ የሚገኘው ማርኪኒሆስ

By Adimasu Aragawu

May 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዚህ ወቅት ዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የመሐል ተከላካዮች መካከል አንዱ ነው ብራዚላዊው የፒኤስጂ ተጫዋች ማርኪኒሆስ፡፡

በፈረንጆቹ 1994 በዛሬዋ ዕለት የተወለደው ማርኪኒሆስ የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው በሀገሩ ክለብ ኮሪንቲያንስ ነው፡፡

ከብራዚሉ ክለብ ኮሪንቲያንስ ጋር የኮፓ ሊበርታዶሬስ ዋንጫ ካሳካ በኋላ የጣሊያኑን ክለብ ሮማ በ3 ሚሊየን ዩሮ ተቀላቅሏል፡፡

ለጣሊያኑ ክለብ ሮማ ለአንድ የውድድር ዓመት ብቻ ተጫውቶ በ2013/14 የውድድር ዓመት በ31 ነጥብ 4 ሚሊየን ዩሮ የፈረንሳዩን ክለብ ፒኤስጂ መቀላቀል ችሏል፡፡

የሀገሩ ልጅ ቲያጎ ሲልቫ ፒኤስጂን በፈረንጆቹ 2020 መልቀቅን ተከትሎ ማርኪኒሆስ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ይገኛል፡፡

ብራዚላዊው የተከላይ ሥፍራ ተጫዋች ማርኪኒሆስ የፓሪሱን ክለብ በአምበልነት እየመራ ፒኤስጂ በ2024/25 በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ሲያሳካ ትልቁን ሚና መወጣቱ ይታወሳል፡፡

ፒኤስጂን ከተቀላቀለ በኋላ እስካሁን ድረስ 10 የሊግ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

በተጨማሪም የአውሮፓ ሱፐር ካፕ እና ሌሎች የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን ከፒኤስጂ ጋር በማሳካት ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል፡፡

ማርኪኒሆስ ዘንድሮም ክለቡ ለአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ለፍጻሜ እንዲደርስም የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡

የፒኤስጂ የኋላ መስመር ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ማርኪኒሆስ በ2024/25 የውድድር ዓመት ለተጋጣሚ ቡድኖች ፈታኝ በነበረው እና በዋንጫ የታጀበ ዓመት ባሳለፈው ቡድን ውስጥ ከማይተኩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡

ፒኤስጂ በአምበሉ ማርኪኒሆስ እየተመራ ለተከታታይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ለማሳካት ከአርሰናል ጋር የሚያደርገው የ90 ደቂቃ ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡

ብራዚላዊው ተጫዋች የኮፓ አሜሪካ፣ የዓለም ክለቦች ዋንጫ እና የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ምርጥ ስብስብ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት መካተት ችሏል፡፡

ማርኪኒሆስ ለፒኤስጂ በሁሉም ውድድሮች እስካሁን ድረስ 521 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን በዚህም በርካታ ጨዋታዎችን ለፓሪሱ ክለብ በማድረግ ቀዳሚው ተጫዋች ነው፡፡

በቀጣይ ተጨማሪ ጨዋታዎችን ሲያደርግ የራሱን በርካታ ጨዋታዎችን ለፒኤስጂ የመጫወት ክብረ ወሰን ከፍ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

ሀገሩ ብራዚልን ከ2013 ጀምሮ ማገልገል የጀመረው ማርኪኒሆስ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን በፈረንጆቹ 2019 ማሳካቱ ይታወሳል፡፡

የብራዚል ብሔራዊ ቡድንን በመወከል በተለያየ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ግልጋሎት ሰጥቷል፡፡

ተጫዋቹ አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ለ2026 ዓለም ዋንጫ ይፋ ባደረጉት 55 ተጫዋቾች ቀዳሚ ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል።

በ2026 ዓለም ዋንጫ ማርኪኒሆስ በብራዚል ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ቁልፍ ከሚባሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ