አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመቅደላ ጦርነት ወቅት በብሪታኒያ የተወሰዱ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት ተመልሰዋል፡፡
ከ158 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ቅርሶቹ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል፣ የልብስ ቁራጮች እንዲሁም የወርቅ አምባር መሆናቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ቅርሶቹ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲመለሱ የተደረገው የኢትዮጵያን የታሪክና የባህል አሻራዎች የማስመለስ ስራ አካል በመሆን ነው፡፡
ለረጅም ዘመናት በባዕድ ሀገር የቆዩት እነዚህ ቅርሶች÷ ኢትዮጵያ የነበራትን ጥንታዊ ስልጣኔና ሉዓላዊነት የሚያሳዩ ትልልቅ የታሪክ ምስክሮች ናቸው ብለዋል።
የቅርሶቹ መመለስ የኢትዮጵያን የታሪክ ባለቤትነትና የዲፕሎማሲ ስኬት የሚያሳይ ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ እንደሚወሰድም ተመላክቷል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ