አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሰባት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል፡፡
ምልዓተ ጉባኤው ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ስለ ሰው ልጅ ሁሉ ደኅንነትና ክብር እንዲሁም ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ነው የተጠናቀቀው፡፡
የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት መጠበቅና ማስጠበቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ተግባር በመሆኑ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊ ክብሯ ተጠብቆ እንድትቀጥል “የሀገራዊ ሰላምና የቤተ ክርስቲያን አንድነት” ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ እና ምርጫው ለኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን የሚያስገኝ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት አሳስቧል፡፡
በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉም ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በአመለወርቅ መኳንንት