ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና በታይዋን ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር ወደ ግጭት ልትገባ ትችላለች – ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ

By Hailemaryam Tegegn

May 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የታይዋን ጉዳይ በአግባቡ ካልተያዘ ከአሜሪካ ጋር ወደ ግጭት ልንገባ እንችላለን አሉ፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ለሁለት ሰዓት የዘለቀ ውይይት አድርገዋል፡፡

ቻይና የሉዓላዊ ግዛቴ አካል ናት የምትላት ታይዋን ሁለቱ መሪዎች በቀዳሚነት ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል አንዷ መሆኗ ተዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንት ሺ የታይዋን ጉዳይ በአግባቡ ካልተያዘ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ወደ ግጭት ልትገባ እንደምትችል አስጠንቅቀው፥ ዋሺንግተን ለደሴቱቱ አስተዳደር የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ መጠን እንድትቀንስ ወይም እንድታዘገይ ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ታይዋንን ከቻይና የመነጠል ሙከራ ከሰላም ጋር የማይታረቅ ነው ሲሉ፥ ታይዋን በበኩሏ ይህ የቤጂንግ አቋም ለቀጣናው ሰላም ጠንቅ ነው ብላለች፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በውይይቱ ላይ በታይዋን ጉዳይ ስለመነጋገራቸው ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በመካከለኛው ምስራቅ እና በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እንዲሁም በኮሪያ ልሳነ ምድር ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የቤጂንግ እና ዋሺንግተን ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፥ የሀገራቱ ስትራቴጂያዊ አጋርነት መጠናከሩን አንስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ማንኛውም አይነት ችግር ቢያጋጥም በአፋጣኝ መፍትሄ ለማበጀት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፥ መጪው ጊዜ ለሀገራቱ መልካም እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ