አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ 29ኛውን የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል ስራ አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ማህበራዊ ፍትህን የምናነግስበት አንዱ የተስፋ ብርሃን የምገባ ፕሮግራማችን ዛሬ በልደታ ክፍለ ከተማ ለክፍለ ከተማው 3ኛ የሆነ 29ኛውን የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል ገንብተን ስራ አስጀምረናል ብለዋል።
በገነባነው 492 ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ 2 ሺህ 460 ለሚሆኑ ነዋሪዎቻችን እፎይታ በሆነው በተለይም በርካታ አረጋውያን፣ ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን እንዲሁም ለልማት ተነሺዎች በሚኖሩበት የበጎነት መንደር ውስጥ ድጋፍ ለሚገባቸው ወገኖች ዛሬ ምገባ ያስጀመርንበት የምገባ ማዕከል ተጨማሪ የበጎነት ስራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ንፁህና ትኩስ ምግብ በቀን አንድ ጊዜ የሚቀርብባቸው በሁሉም ክፍለ ከተማ 29 የምገባ ማዕከላት ውስጥ መመገብ ስለሚቻል ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችን ምግብ ፍለጋ ወደ ጎዳና የሚያስወጣ ምክንያት በከተማችን ስለሌለ፤ በማዕከላቱ በመገኘት መመገብ ትችላላችሁም ነው ያሉት።
በበጎነት መንደሩ የስራ እድል የተፈጠረባቸው የእንጀራ መጋገሪያ ማዕከል፣ የልብስ ስፌት፣ የፀጉር ስራና የልጆች መጫወቻ ለነዋሪዎቹ ሌላኛው የእፎይታ ምንጭ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩን ጥሪ ተቀብሎ ለማዕከሉ ግንባታ እና በቀጣይም ለመመገብ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለተወጣው ዳሽን ባንክ ምስጋና አቅርበዋል፡፡