አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ስፔናዊው አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ለተከታታይ 3ኛ የውድድር ዓመት ከፒኤስጂ ጋር የፈረንሳይ ሊግ ዋንጫን ማሸነፍ ችለዋል፡፡
በፈረንጆቹ 1970 ስፔን ውስጥ በዛሬው ዕለት የተወለዱት አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ የአሰልጣኝነት ስራቸውን የጀመሩት በባርሴሎና ቢ ቡድን ነው፡፡
ከባርሴሎና ቢ ቡድን በመቀጠል ሮማ እና ሴልታቪጎን ያሰለጠኑት አሰልጣኙ በፈረንጆቹ 2014 የባርሴሎና ዋናውን ቡድን ተረክበዋል፡፡
በካታላኑ ክለብ ባርሴሎና በነበራቸው የአሰልጣኝነት ቆይታ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ የስፔን ላሊጋ፣ የስፔን ሱፐር ካፕ፣ ኮፓ ዴል ሬይ፣ የዓለም ክለቦች ዋንጫ እና የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን አሳክተዋል፡፡
ከባርሴሎና ጋር ከተለያዩ በኋላ የስፔን ብሔራዊ ቡድንን ከፈረንጆቹ 2018 እስከ 2022 አሰልጥነው በ2023/24 ወደ ፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ አቅንተዋል፡፡
የፓሪሱን ክለብ በ2023/24 ከተረከቡ ወዲህ የዘንድሮን ጨምሮ ለተከታታይ ሦስት የውድድር ዓመታት የሊጉን ዋንጫ ማሳካት ችለዋል፡፡
ፒኤስጂ በታሪኩ 14ኛ የፈረንሳይ ሊግ ዋንጫውን ያሳካ ሲሆን÷ በኤንሪኬ እየተመራ ደግሞ ያለፉትን ሦስት ተከታታይ የውድድር ዓመት ሻምፒዮን ሆኗል፡፡
ፒኤስጂ በሀገር ውስጥ ውድድር ስኬታማ ቢሆንም በአውሮፓ መድረክ ግን ተፎካካሪ ለመሆን እና ዋንጫ ለማንሳት የኤንሪኬን ፓሪስ መድረስ ይፈልግ ነበር፡፡
ፒኤስጂ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ለማሳካት ሊዮኔል ሜሲ፣ ኔይማር ጁኒየር እና ኪሊያን ምባፔ የመሳሳሉ ተጫዋቾችን ቢያጣምርም ማሳካት እንዳልቻለ ይታወቃል፡፡
ከስፔናዊው አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ፓሪስ መድረስ በኋላ ግን የክለቡ የዘመናት ጥያቄ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ምላሽ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ የፈረንሳዩን ክለብ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የዘመናት ሕልም መፍታት የቻሉ ሰው ናቸው፡፡
ፒኤስጂ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን በፈረንጆቹ 2024/25 የውድድር ዓመት ሲያሳካ አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ በክለቡ ያመጡት ለውጥ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
አሰልጣኙ በአንድ ተጫዋች ላይ ጥገኛ ያልሆነ እንደ ቡድን የሚጫወት ጠንካራ ስብስብ በመገንባት ክለቡን ለዚህ ታላቅ ክብር አብቅተዋል፡፡
አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ አሁን የፈረንሳዩን ክለብ ፒኤስጂን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ ለተከታታይ የውድድር ዓመት ለፍጻሜ ማድረስ ችለዋል፡፡
የአሰልጣኝ ኤንሪኬ ቡድን በዚህ የውድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተጋጣሚዎቹ ላይ 44 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን÷ በዚህም በውድድር ዘመኑ በመድረኩ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚው ሆኗል።
ቡድኑ በዚህ የውድድር ዓመት በመድረኩ ባየርን ሙኒክ፣ ሊቨርፑል፣ ቼልሲ እና ባርሴሎናን የመሳሰሉ ቡድኖችን ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ፒኤስጂ በአሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ እየተመራ ለተከታታይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ያሳካ ይሆን የሚለው የሚጠበቅ ሲሆን÷ በፍጻሜው ከአርሰናል ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ግንቦት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በሀንጋሪ ቡዳፔስት ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም ይደረጋል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ