አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አርሰናል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ38 ጨዋታዎች ውድድር አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ የወርቅ ዋንጫ ባለቤት መሆን የቻለ ብቸኛ ክለብ ነው።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ “ዘ ኢንቪንስብል” (የማይበገሩት) በመባል ይህን ደማቅ ታሪክ የጻፈው ከ22 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ዕለት ነበር።
በወቅቱ በፈረንሳዊው አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር የሚመሩት መድፈኞቹ በሊጉ እስከዛሬም ድረስ ለሌሎች ክለቦች ያልተቻለውን ይህን ስኬት በ2003/4 የውድድር ዓመት አሳክተውታል።
በውድድር ዓመቱ በሊጉ ካደረጓቸው 38 ጨዋታዎች በ26ቱ ድል አድርገው በ12ቱ አቻ የተለያዩ ሲሆን፥ 90 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከተከታያቸው ቼልሲ በ11 ነጥብ ርቀው ሻምፒዮን ሆነዋል።
ከአርሰናል አስቀድሞ በፈረንጆቹ 1888/9 ምንም ጨዋታ ባለመሸነፍ “ዘ ኢንቪንስብል” የሚል ማዕረግ ያገኘው ፕሪስተን ኖርዝ ኢንድ ነበር።
ሆኖም በወቅቱ በሊጉ በአንድ የውድድር ዓመት 27 ጨዋታዎች ብቻ ይደረጉ ስለነበር በ38 ጨዋታዎች ውድድር ይህን ያሳካ ብቸኛ ክለብ አርሰናል ሆኖ በታሪክ ሰፍሯል።
አርሰናል በዚያ የውድድር ዓመት አራት ጨዋታዎች እየቀሩት አስቀድሞ የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን፥ ያለመሸነፍ ጉዞው ሊገታ የተቃረበባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።
በተለይም ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር ያለ ግብ አቻ ሆነው 90 ደቂቃ ከተጠናቀቀ በኋላ በባከነ ደቂቃ የፍጹም ቅጣት ምት የተሰጠባቸው አጋጣሚ ይታወሳል።
ሆኖም የሩድ ቫን ኒስትሮይ የፍጹም ቅጣት ምት ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሶ መድፈኞቹ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ከመሸነፍ የተረፉበት አጋጣሚ አይዘነጋም።
በተመሳሳይ ከሊጉ ላለመውረድ በሚጫወተው ሌስተር ሲቲ 1 ለ ዐ ከመመራት ተነስተው 2 ለ 1 ያሸነፉበት የመጨረሻ ሳምንት መርሐ ግብር የወርቅ ዋንጫውን ሊያጡ የተቃረቡበት አጋጣሚ እንደነበር ይጠቀሳል።
ጀርመናዊው ግብ ጠባቂ የንስ ሌማን 21 ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ችሏል።
ለዚህም በሶል ካምቤል እና ኮሎ ቱሬ የሚመራው የመድፈኞቹ የተከላካይ መስመር ሚና ከፍተኛ ነበር።
በ30 ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው ቲየሪ ሄንሪ የፕሪሚየር ሊጉ ዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመባል የተሸለመበት ዓመት ነበር።
ከሄንሪ በተጨማሪ ዴኒስ ቤርካምፕ፣ አማካዩ ፓትሪክ ቪዬራ እና የግራ መስመር ተከላካዩ አሽሊ ኮል ከዚያ ወርቃማ ስብስብ ውስጥ የሚጠቀሱ ተጫዋቾች ናቸው።
በ2002/3 የውድድር ዓመት የተጀመረውና እስከ 2004/5 የውድድር ዓመት የዘለቀው የመድፈኞቹ የ49 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ በፈረንጆቹ ጥቅምት 2004 በማንቼስተር ዩናይትድ መገታቱ አይዘነጋም።
የሰሜን ለንደኑ ከዚያ ታሪካዊ ድል በኋላ ያላገኘውን የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ከ22 ዓመታት በኋላ ለማጣጣም ከጫፍ ደርሷል።
አርሰናል ከሁለት አስርት ዓመታት የተሻገረውን የሊግ ዋንጫ ጥም ለመቁረጥ ከበርንሌይ እና ክሪስታል ፓላስ ጋር የሚያደርጋቸውን ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ማሸነፍ በቂው ነው።
በኃይለማርያም ተገኝ