ጤና

ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት የትምባሆ ቁጥጥር …

By Yonas Getnet

May 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ኢትዮጵያ በትምባሆ ቁጥጥር ተጨባጭ ውጤት አስመዝግባለች አለ።

የዓለም ከትምባሆ ጭስ ነፃ ቀን በዓለም ለ39ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ ”ለኒኮቲንና ለትምባሆ ሱሰኝነት አጋላጭ የሆኑ ስልቶችን እናጋልጥ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው።

ባለስልጣኑ ቀኑን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ ትምባሆ ቁጥጥር ላይ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብሏል፡፡

በዚህም በ8 ክልሎች የትምባሆ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ማቋቋምና የማጠናከር ስራዎች መሰራታቸው ተጠቁሟል፡፡

ወደ 900 ሺህ የሚጠጉ ተቋማት ከትምባሆ ጭስ ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ፍተሻ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ ለተቋማቱ ባለቤቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ለማጨስ ሊውሉ ይችሉ የነበሩ የትምባሆ ቅጠል እና ሲጋራዎችን ማስወገድ መቻሉን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

የዘንድሮውን የዓለም ከትንባሆ ነጻ ቀን ሲከበር የኒኮቲን እና የትንባሆ ሱስን በጋራ ለመመከት ቃል በመግባት እንደሆነም አመልክቷል።

የቁጥጥር ሕጎችን እና የፖሊሲ ክፍተቶችን በመድፈን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ንቅናቄውን እንዲያጠናክሩ ጠይቋል።

መገናኛ ብዙኃን የኢንዱስትሪውን አሳሳች ማስታወቂያዎች በማጋለጥና ትክክለኛውን የጤና መረጃ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።