አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሮቤ ከተማ አስተዳደር 12 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በመጀመሪያው ዙር ሥራ ተከናውኗል፡፡
የከተማዋ ከንቲባ ዲኖ አሚን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለፁት ÷ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን የምታስተናግደው ሮቤ ከተማ በኮሪደር ልማት አዲስ ገፅታ እየተላበሰች ነው።
ከንቲባው በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የብስክሌት እና የእግረኛ መንገድ፣ የመንገድ ዳር መብራቶች እና አረንጓዴ ስፍራዎች ያሉት ነው ብለዋል።
ኮሪደር ልማቱ ቴሌ፣ ውሃ እና መብራት ኃይሎች ተናበው የሚሰሩበትን ሥርዓት ያካተተ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
እነዚህ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ከማዘመን በተጨማሪ የከተማዋን ነዋሪዎች ኑሮ የቀየሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱ የሥራ ባህልን የቀየረ እና በከተማዋ የሚገኙ ተቋማት በምሽት እንዲሰሩ ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ ሥራ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።