የሀገር ውስጥ ዜና

የእኛ ሕልም ሀገርን ከድህነት የሚያላቅቅ ትውልድ መፍጠር ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

May 16, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእኛ ፍላጎትና ሕልም ከድህነትና ከችግር የተላቀቀች ሀገር የሚፈጥር ትውልድ መፍጠር ነው አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክን የመጀመሪያ ምዕራፍ በዛሬው እለት መርቀው ከፍተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዓለም በኢትዮጵያ እየተደነቀና እየቀና ባለበት ጊዜ ዐይናችን ከታወረ ለማደግ እንቸገራለን ብለዋል፡፡

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ራሱን ችሎ ሌሎች ወንድሞቹን ማገዝ የሚችልበት ደረጃ ድረስ ማደግ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡

ይህ እንዲሳካ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተባበር እንዳለበት ጠቅሰው፥ ካልሰራን ሀገር ስለማይለወጥ ኢትዮጵያን በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እዚህ አካባቢ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልጸው ሌሎች አካባቢዎች ላይ እየሰራን ስንሄድ ሀገር ይቀየራል ነው ያሉት፡፡

አርሶ አደሮችንና ደሀን በመጣልና እጅ አጠሮችን በመግፋት የሚሰራ ልማት የትም አያደርሰንም ብለዋል፡፡

ችግርና ድህነት መጥፎ ነው፥ የሰው እጅ ማየት በግለሰብም እንደ ሀገርም አስቀያሚ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከዚያ ወጥቶ ራስን ለመቻል በመተባበር መትጋት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ