የሀገር ውስጥ ዜና

አስተማማኝ ኢንዱስትሪን ለመገንባት በተናጠል ሳይሆን በመሰናሰል መስራት አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

May 16, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተማማኝ ኢንዱስትሪን ለመገንባት በተናጠል ሳይሆን ተደምረን በመሰናሰል መስራት አለብን አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት ‎የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት፥ ኢንዱስትሪዎች ሲቋቋሙ በአካባቢዎቹ ያሉ ነዋሪዎችን የሚጠቅሙ ሊሆኑ ይገባል፡፡

በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በፓርኩ ስራ የጀመሩ ወጣቶች ከጥቂት ዓመታት በፊት ስራ እንዳልነበራቸው አስታውሰው፥ አሁን ላይ ሌሎችን ቀጥረው ሲሰሩ መመልከት ደስታ ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አልሚዎች መፍለቂያ እንደሚሆን ገልጸው፥ ሁሉም ክልሎች ከዚህ ፓርክ ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ለግብርና ስራ የሚውል ፓምፕ፣ የወርቅ ማምረቻ፣ የመኖ ማቀነባበሪያ እና የብሎኬት ማምረቻ ፋብሪካ ማሽኖች እንደሚመረቱ ጠቁመዋል፡፡

ፋብሪካን ማምረት ለሚችሉ ወጣቶች የሚደረግ ማንኛውም ድጋፍ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፥ አሁን ላይ በመጠኑ የተደረገላቸው ድጋፍ ይህንን ውጤት አስገኝቷል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ቀደም በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተሰማርተው የነበሩ የውጭ ሀገራት አልሚዎች የአጎዋ ችግር ሲፈጠር ጥለው መሄዳቸውን ተከትሎ ፓርኩ ከ80 በመቶ በላይ ክፍት ሆኖ መቅረቱን አስታውሰዋል፡፡

ከውጭ የሚመጡ አልሚዎች የሚወስዱትን ወስደው እንደሚሄዱ ጠቅሰው፥ የእኛን ኢንዱስትሪ በእኛው ሀገር ሰዎች እንዲሰራ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን አስተማማኝ ኢንዱስትሪን ለመገንባት የእውቀት ሽግግርና ካፒታል አስፈላጊ በመሆኑ ከውጭ የሚመጡትን ከመግፋት ይልቅ ከሀገር ውስጥ አልሚዎች ጋር በማሰናሰል መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የተናጠል ኢንዱስትሪ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ከማሟላት አንጻር አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ምቹ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዲቻል በመደመር መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ