አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን ጉልበትና ሀገር በቀል ዕውቀት በመጠቀም፣ በአነስተኛ ወጪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በሐረሪ ክልል የተመለከትነው የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ በመቀየሩ ረገድ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ዋና ዓላማ የገጠር ማኅበረሰብን የኑሮ ዘይቤ መቀየር፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም አርሶ አደሩ የተሻለ ሕይወት እንዲመራ ማስቻል መሆኑን አመልክተዋል።
በሶፊ ወረዳ ቡርቃ ቀበሌ በፍጥነት፣ በጥራትና የአካባቢውን አፈርና ድንጋይ በመጠቀም በሕብረተሰቡ እውቀት የተሠሩ ሥራዎች ለዚህ ትልቅ ማሳያ መሆናቸውን ተመልክተናልም ነው ያሉት።
በሞዴል መንደሩ የተገነቡት ቤቶች የሰዎችን ማደሪያ ከሕፃናትና ከከብቶች ቤት የለዩ፣ የዶሮ እርባታ፣ ሻወርና ሽንት ቤት እንዲሁም የጓሮ የሌማት ትሩፋትን ያካተቱ ሙሉ ፓኬጅ እንዳላቸውም አብራርተዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን ጉልበትና ሀገር በቀል ዕውቀት በመጠቀም በአነስተኛ ወጪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ገልጸዋል።