አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካርጎ፣ በአቪዬሽን አካዳሚ ማሰልጠኛ እና በሌሎችም የዘርፉ አገልግሎቶች አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነ ነው አሉ የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው።
አየር መንገዱ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት አስመልክቶ ያዘጋጀው የ8 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እየተካሄደ ነው።
አቶ መስፍን ጣሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አየር መንገዱ ባከናወናቸው ተግባራት ከአፍሪካ ቀዳሚና ግዙፍ የአየር መንገድ መሆን ችሏል።
አየር መንገዱ በሚያደርገው ያልተቋረጠ እድገት የዓለምን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያካተቱ የተለያዩ የቦይንግ፣ የኤርባስ እና የሌሎች አውሮፕላኖች ባለቤት መሆን እንደቻለ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ145 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እንዳሉት ጠቁመው÷ በተለያዩ የዘርፉ አገልግሎቶች አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
አየር መንገዱ የ80 ዓመታት የስኬት ጉዞው የጎዳና ላይ ሩጫን ጨምሮ በፓናል ውይይቶች፣ በአውደ ርዕዮች እና በተለያዩ ማህበራዊ ዝግጅቶች በታላቅ ድምቀት እያከበረ ይገኛል።
በዛሬው የሩጫ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን፣ የአየር መንገዱ የሥራ ኃላፊዎች እና አትሌቶች ተገኝተዋል።