የሀገር ውስጥ ዜና

የማዳበሪያ ፋብሪካው የሥራ ሂደት ፍጥነት አበረታች ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Adimasu Aragawu

May 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓመት 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ያለው የማዳበሪያ ፋብሪካ የሥራ ሂደት ፍጥነት አበረታች ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ዛሬ ማለዳ ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመሆን በጎዴ ተገኝቼ ሥራው የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገም የፕሮጀክት ስፍራውን ጎብኝቻለሁ ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመሆን በዓመት 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ያለውን ፋብሪካ ለማቋቋም ትልቅ የባለድርሻ ስምምነት አድርገን ነበር በማለት አስታውሰዋል።

በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ደግሞ የፕሮጀክቱን ግንባታ በይፋ ጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህ ሥራ ከመሠረተ ልማት ግንባታም በላይ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የኢንዱስትሪ እድገት እና በኢኮኖሚ ራስ የመቻል ጥረት ውስጥ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ኢንቨስትመንት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የማዳበሪያ ፋብሪካው በሚጠናቀቅበት ወቅት የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ያጎለብታል፣ ከውጭ በሚገባ ማዳበሪያ ላይ ያለውን ጥገኝነት ይቀንሳል፣ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አርሶአደሮቻችንን ይደግፋልም ነው ያሉት።

ለኢንቨስትመንት እና የሥራ ዕድል ፈጠራም አዳዲስ እድሎችን እንደሚከፍት አስረድተዋል።

በመላው የፕሮጀክቱ ስፍራ የሚታየው የሥራ ሂደቱ ፍጥነት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ግዙፍና እጅግ ጠቃሚ ሀገራዊ ፕሮጀክት ለመፈፀም ያለውን ቁርጠኝነትና ትብብር በሚያንፀባርቅ ሁኔታ በተለያዩ የፕሮጀክቱ ክፍሎች ያሉት ግንባታዎች በእቅዳችን መሠረት እየተጓዙ ይገኛሉ ብለዋል።