አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአጭር ጊዜ ውስጥ የጎዴ የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቅቆ የኢትዮጵያ አንዱ ቁልፍ ችግር ይፈታል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎዴ ተገኝተው የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ጎብኝተዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር የነበረን ስምምነት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ምርትን መጨመር አንዱ አንጓ ነበር ብለዋል።
ሁለተኛው ደግሞ በጎዴ በዓመት 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ያለው የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት መሆኑን አንስተዋል።
በወቅቱ ለሕዝብ የገነባው ቃል በ40 ወራት ውስጥ የፋብሪካው ግንባታ ይጠናቀቃል የሚል ነበር ሲሉም ገልጸዋል።
ይህንን ሥራ ከጀመርን በኋላ በዓለም ላይ ማዳበሪያ እና ነዳጅ በጣም አስፈላጊ ሆኖ ስለመጣ ጊዜውን ለማሳጠር ከዳንጎቴ ጋር ስንመካከር ቆይተዋልም ነው ያሉት።
በዚህም ከ40 ወራት በፊት ሥራውን ጨርሰን ምርቱን ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ ለመጠቀም ተስማምተናል ብለዋል።
ሥራው በፍጥነት ተጠናቅቆ ከ4 ወራት በኋላ ተመልሰን እንመጣለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ተመልሰን ስንመጣ፤ በአካባቢው ለ5 ሺህ ሰዎች የሚሆን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ይጠናቀቃል ሲሉም ተናግረዋል።
በአጭር ጊዜ የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቅቆ የኢትዮጵያ አንዱ ቁልፍ ችግር እንደሚፈታ አመልክተዋል።
በጎዴ አካባቢ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ደረጃ ከፍተኛ ገቢ ለኢትዮጵያ የሚያስገኙ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በምግብ ራስን መቻል ዋነኛ አጀንዳችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ በምግብ ራስን ለመቻል መሬት፣ ውሃ እና ሰው እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
እነዚህ ሁሉም አሉን፤ እነዚህን አቀናጅተን ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ እየሰራን እንገኛለንም ነው ያሉት።
በዚህም ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የሚተርፍ ነገር ማድረግ እንችላለን ብለዋል።
በብርሃኑ አበራ