አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 24ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በሚደረጉ ውድድሮች ይጠናቀቃል።
በውድድሩ የመጨረሻ ቀን ላይ ኢትዮጵያን የወከሉ አትሌቶች የሚካፈሉባቸው 8 የፍፃሜ ውድድሮች ምሽት ላይ ይደረጋሉ።
በዚህም አመሻሽ 12:30 ላይ በከፍታ ዝላይ አትሌት ገመዶ አባተ እንዲሁም አመሻሽ 12:40 አትሌት ኦታጌ ኦባንግ በወንዶች የጦር ውርወራ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።
ምሽት 1 ሰዓት ላይ ደግሞ በ3 ሺህ ሜትር የሴቶች መሰናክል ሩጫ ላይ አትሌት ወሰኔ አሰፋ እና አትሌት አልማዝ ዮሐንስ የሚሳተፉ ሲሆን÷ ምሽት 1:20 ላይ ደግሞ በ400 ሜትር የሴቶች መሰናክል አትሌት ደራርቱ እኖታ፣ አትሌት እመቤት ተከተል እና አትሌት ባንቻየሁ ተሰማ ኢትዮጵያን ይወክላሉ።
እንዲሁም ምሽት 1:50 ላይ የ1 ሺህ 500 ሜትር የሴቶች ሩጫ አትሌት አዳኑ ኔንቆ፣ አትሌት ማህተቤ ፍቃዱ እና አትሌት ደስታ ታደለ ተሳታፊ ናቸው።
ምሽት 2 ሰዓት ላይ የ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ሩጫ አትሌት እንዳሻው ረታና አትሌት አሸናፊ ኢማና ሲካፈሉት÷ ምሽት 2:20 ላይ ደግሞ በ5 ሺህ ሜትር የወንዶች ሩጫ አትሌት ሙቢን ሀጂ፣ አትሌት ጀምበሩ ሲሳይ እና አትሌት ገብሩ አብረሃ ተፋላሚ ናቸው።
በመጨረሻም ምሽት 3 ሰዓት በ400 ሜትር የሴቶች ሩጫ አትሌት ገነት አየለ፣ አትሌት ምስጋና ኃይሉ፣ አትሌት ትዕግስት አያና እና አትሌት አጃይባ አልዪ ይወዳደራሉ።
በውድድሩ ኢትዮጵያ እስካሁን 11 ሜዳሊያዎች አስመዝግባለች።
በወርቅነህ ጋሻሁን