የሀገር ውስጥ ዜና

የመዲናችን የብልጽግና ጉዞ የሚለካው ያልተጠቀምንባቸውን ሀብቶች የልማት ማዕከል በማድረግ ጭምር ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Yonas Getnet

May 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመዲናችን የብልጽግና ጉዞ የሚለካው ያልተጠቀምንባቸውን ሀብቶች የልማት ማዕከል በማድረግ ጭምር ነው አሉ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ‘ገላን ጉራ የብልጽግና አሻራ!’ በሚል ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመዲናችን የብልጽግና ጉዞ ስፋትና ጥልቀት የሚለካው የከተማዋን እምብርት በማስዋብ ብቻ ሳይሆን፣ ትናንት በአግባቡ ያልተጠቀምንባቸውን ሀብትና አካባቢዎችን ዓይናችንን ገለጥ በማድረግ ተመልክተን የልማትና የዕድገት ማዕከል በማድረግም ጭምር ነው ብለዋል።

ከ5 ዓመት በፊት ምንም የሚታይ መሠረተ ልማት ያልነበረው የገላን ጉራ አካባቢ ዛሬ ላይ የታሪክ ምዕራፉ ተቀይሮ የከተማችንን ሁለንተናዊ የልማት ከፍታና መዋቅራዊ ሽግግር የሚያሳይ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መስተጋብር ማዕከል ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።

ዛሬ በዚህ ስፍራ ያረፈው አሻራችን የኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ገጽታ እና የነዋሪዎቹን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ከስር መሠረቱ የለወጠ ነው በማለት ተናግረዋል።

ለአብነትም:-

1. በአዲስ አበባ የመጀርያው እና ትልቁ ባለ 325 ሜትር ርዝመት እና 60 ሜትር ስፉት ዘመናዊ ድልድይ፣

2. 21.73 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው (ቃሊቲ ቀለበት -ቱሉዲምቱ እና ቃሊቲ ቀለበት – ቂሊንጦ አደባባይ) የኢትዮጵያ የንግድ ኮሪደርን ያሳለጠ እና ቀጥታ ከአየር መንገድ ካርጎ የሚያገናኝ ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማት፣

3. የከተማችንን የመኖርያ ቤት አቅርቦት ችግር ለማቃለል አዲስ ከተማን የመገንባት ያህል የሆነ 60 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣

4. ከካዛንቺስ አካባቢ ለልማት ለተነሱ ነዋሪዎቻችን የገነባነው ምቹና የተቀናጀ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር የሚገኝበት፣

5. የኅብረተሰባችንን ጤና በላቀ ደረጃ ለመጠበቅ በከተማችን በትልቅነቱ ቀዳሚ የሆነው የገላን ትሯማ ሆስፒታል ግንባታ፣

6. በአካባቢው ለዚሁ ልማት ለእርሻ ሲጠቀሙበት የነበረውን መሬት ለለቀቁልን አርሶ አደሮች የተቀናጀ ዘመናዊ የግብርና ልቀት ማዕከል ግንባታ፣

7. መንፈስን የሚያድሱ ሰፋፊ አረንጓዴ ስፍራዎች እና ፓርኮች እንዲሁም

8. የስፖርት ማዘውተርያዎችና የልጆች መጫወቻዎች፣ ለእናቶች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥር የእንጀራ ፉብሪካ ግንባታ እና የመሳሰሉት የብልፅግና አሻራዎች ደምቀው አካባቢውን ከመሐል ከተማ የበለጠ ተመራጭ አድርገውታል ብለዋል በመልዕክታቸው።