የሀገር ውስጥ ዜና

የዓለም የሙዚየም ቀን በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ነው

By Yonas Getnet

May 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም የሙዚየም ቀን “ሙዚየሞች የተከፋፈለውን ዓለም ያስተሳስራሉ” በሚል መሪ ቃል በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ24ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን የዓለም ሙዚየም ቀን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ቢኒያም ታዬ÷ ሙዚየሞች ትናንትን ከዛሬ የሚያገናኙ ድልድዮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

አዲስ አበባ ቅርሶችን በማልማትና በማደራጀት የቱሪዝም መስህብ እንዲሆኑ እያደረገች መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው÷ ሙዚየሞች ባህልንና ህዝብን ለማቀራረብ አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

ቅርሶችን የመዝናኛ እና የመረጃ ምንጭ በማድረግ ትውልድን የሚገነቡ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤካ (ዶ/ር)÷ ሙዚየሞች የዓለም ማህበረሰብን የሚያስተሳስሩ መልህቅ መሆናቸውን አብራርተው፤ የጋራ ታሪክና የወል ትርክት የምንገነባባቸው መሰረቶች ናቸው ብለዋል።

በቅድስት አባተ