አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለንተናዊ የልማት አቅጣጫ በሚበየንበት ጠቅላላ ምርጫ ላይ ካርድ የወሰዱ ዜጎች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሀገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታና ሁለንተናዊ የልማት አቅጣጫ የሚበይን መሆኑ ተገልጿል።
ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት የሀገር ሽማግሌ በለጠ ባሹ፤ የሀገር ሽማግሌዎች ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነጻና ገለልተኛ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ይህ ማለት ግን የሀገርን ቀጣይ እጣ ፈንታ በሚወስን ምርጫ አይሳተፉም ማለት እንዳልሆነ ገልጸው፤ ሁሉም ዜጎች በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
በመሆኑም መንግሥት ለሀገር ዘብ መሆኑን መረዳት እንደሚገባ በማንሳት፤ በምርጫ ሂደት አለመሳተፍ ቤትን ያለ በርና ያለ ጠባቂ እንደመተው ይቆጥራል ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም ሕብረተሰቡ የሀገርን ሉዓላዊነትና እድገት የሚያስቀጥል ፓርቲን በጥንቃቄ ለይቶ በመምረጥ ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አመላክተዋል።
አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ከፍታ በየዘርፉ የሚያስቀጥል ፓርቲን ለመምረጥ እያንዳንዱ ዜጋ መሳተፍ አለበት ብለዋል።
እያንዳንዱ መራጭ መብቱንና ሰላሙን ጠብቆ ድምፁን መስጠት እንዳለበት ገልጸው፤ ሀገርን የሚያስቀጥል መንግሥት ለመመስረት ሕብረተሰቡ በንቃት መሳተፍ አለበት ነው ያሉት።
ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሚናውን መወጣት እንዳለበት እና ኃላፊነትን ለሌላ አካል ብቻ መተው እንደማይገባ ያስገነዘቡት ደግሞ አቶ አብዱል መሀሙድ ናቸው።
ማህበረሰቡ ይሆነኛል የሚለውን ለመምረጥ ከመውጣት ባለፈ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን ለምርጫው መሳካት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን ገልጸው፤ ዜጎች ለሀገርና ለትውልድ የሚበጀውን እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት