የሀገር ውስጥ ዜና

ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የዳታ ሉዓላዊነት ወሳኝ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

May 18, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እና የፖሊሲ ነጻነትን ለማረጋገጥ የዳታ ሉዓላዊነት ቁልፍ እና መሰረታዊ ጉዳይ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ‎”የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በሚል መሪ ሀሳብ ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ባስመዘገበችው ስኬት ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ጉባኤ ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያን የዳታ የመሰብሰብ፣ የማደራጀትና የመተንተን አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ የዘርፉን ሙያተኞች አመስግነዋል።

ሉዓላዊነት የሀገርን ድንበርና አካላዊ አቅምን መከላከል ብቻ ሳይሆን የዳታ፣ የምግብ እና የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥም ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይም የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የራስን የዳታ ምንጮች ማመንጨት እንጂ ዳታ ሸምቶ መመራት እንደማይቻል አስገንዝበዋል።

ከውጭ የተገኘ ወይም የተዋሰ ዳታ የሀገርን ተጨባጭ መሻት፣ ፍላጎትና የወደፊት ትልም በተሟላ መንገድ ሊያሳካ እንደማይችል በማንሳት ለዚህም የራስን ዳታ በተለያዩ መንገዶች ማሰባሰብ፣ ማከማቸትና መተንተን መቻል ለፖሊሲ ሉዓላዊነት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን አቅም በትክክል ካላወቀች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ ምዘና፣ ለድርድር፣ ለውጭ ኢንቨስትመንት ሳቢነትና ለብድር አቅርቦት ጭምር አዳጋች እንደሚሆንባት ገልጸው፤ የዳታ ሉዓላዊነት በግልጽነትና በእኩልነት እንድትገናኝ ያደርጋታል ነው ያሉት።

የዳታ ምንጭ አንድ ብቻ ሲሆን የመረጃ ጥራት ላይ የሚያስከትለው አደጋ እንዳለ ተናግረዋል።

በተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ መንገዶች መረጃን ለመሰብሰብ መቻል የዳታ ጥራት ያደገ እንዲሆን ያስችለዋልም ነው ያሉት።

ከብዙ ዳታ ምንጭ በብዙ መንገድ ዳታ በማሰባጠር እና በመተንተን የጠራ መረጃ ለማግኘት ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት