የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ 120 ሚሊየን የሻይ ቅጠል ችግኝ ይተከላል

By Yonas Getnet

May 18, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 120 ሚሊየን የሻይ ቅጠል ችግኝ ይተከላል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ እየተከናወነ የሚገኘውን የሻይ ቅጠል ልማት ተመልክተዋል።

አቶ ጌቱ ገመቹ በወቅቱ እንዳሉት፤ ክልሉ ሻይ ቅጠልን ጨምሮ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበርክቱ የግብርና ኢኒሼቲቮችን እየተገበረ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ የለሙ የሻይ ቅጠል ተክሎች ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ መሆናቸውን አንስተው፤ በዘንድሮ መርሐ ግብር 120 ሚሊየን የሻይ ቅጠል ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።

በጅማ፣ ቡኖ በደሌና ኢሉአባቦር ዞኖች ብቻ 3 ሺህ 400 ሄክታር መሬት በሻይ ቅጠል ተክል ለማልማት ታቅዶ የጉድጓድ እና የችግኝ ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል።

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ትጃኒ ናስር በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተተከሉት የሻይ ቅጠል ችግኞች መጽደቃቸውን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት 1 ሺህ 728 ሄክታር መሬት በዘርፉ ለማልማት መታቀዱን አመልክተዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ለምርቱ ማቀነባበሪያ የሚሆኑ ማሽነሪዎችን ለመትከል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአሚና አብደላ