አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከዓለም አቀፉ የከተሞች ፎረም ጎን ለጎን በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ያደረግነው ጉብኝት ለከተሞቻችን ልማት ትልቅ ልምድ የቀሰምንበት ነው አሉ፡፡
በፎረሙ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ በባኩ ከተማ የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎችን እና የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው እንዳሉት፥ የባኩ ከተማ የከተማ እድሳት ሂደት የአዲስ አበባን እና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችን ተሞክሮ የሚያንፀባርቅ ነው።
ጉብኝቱ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የጀመርናቸውን የከተማ ልማት፣ የቅርስ እድሳትና ጥበቃ ስራዎችን ይበልጥ አጠናክረን እንድንቀጥል ተጨማሪ ትልቅ ልምድ የተቀሰመበት ነው ብለዋል።
አሮጌና ጎስቋላ የነበረውን ስፍራ ሙሉ በሙሉ በማፍረስና እንደ አዲስ በመገንባት እንዲሁም ጥንታዊቷ ከተማ በመባል የሚታወቀውን የከተማዋ ክፍል በጥንቃቄ በማደስ ለጉብኝት ክፍት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ይህ የከተማ እድሳት ሂደት የኢትዮጵያን ተሞክሮ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ገልጸው፥ ታሪክና ቅርሶችን ጠብቆ በማደስ ጎስቋላ አካባቢዎችን በአዲስ መልክ እየገነባን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ለአብነትም በፒያሳ እና አራት ኪሎ ያሉ ጥንታዊ ሕንፃዎችን፣ የመጀመሪያውን ሲኒማ ቤት፣ የመጀመሪያውን ማዘጋጃ ቤት፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን እንዲሁም የተለያዩ ሐውልቶችን እድሳት ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር እንደ ሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጎንደር ፋሲል ቤተ መንግሥት የመሳሰሉትን ታላላቅ ቅርሶች በማደስ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
እጅግ ጎስቋላና ለመኖር ምቹ ያልነበሩ መንደሮችን በማፍረስ ዘመናዊና ምቹ በሆነ መልኩ መገንባታቸውን ጠቅሰው፥ በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች በተሳካ ሁኔታ የተተገበረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የዚሁ ራዕይ ዋነኛ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ይበልጥ ምቹ፣ ማራኪ፣ አረንጓዴና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በማስፋት፣ ለእግረኛና ለብስክሌት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን በመፍጠር እንዲሁም የከተማዋን ገጽታ በመቀየር እጅግ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት።