የሀገር ውስጥ ዜና

ዳታን ለሀገራዊ ዕድገት መጠቀም ይገባል – ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)

By Adimasu Aragawu

May 19, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዳታን ለሀገራዊ ዕድገት መጠቀም ይገባል አሉ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፡፡

”የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በሚል መሪ ሐሳብ ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ባስመዘገበችው ስኬት ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ጉባኤ ተካሂዷል።

ዋና ዳይሬክተሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና ዳታን ዘርፋቸው ላይ የሚጠቀሙ ተቋማት የማምረት አቅማቸው እየጨመረ ነው፡፡

አፍሪካ ዳታ ላይ በስፋት መስራት እንዳለባት አንስተው÷ አፍሪካውያን በዘርፉ ግንዛቤ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ አገልግሎት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ኢነርጂ እና ቴሌኮም ዘርፎች ከፍተኛ የዳታ ምንጭ ሆነዋልም ነው ያሉት፡፡

ሀገራት ዳታን ለአሁኑ ዘመን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ ተንትነው በማስቀመጥ ትልቁ መወዳደሪያቸው አድርገው እየሰሩበት ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የአገልግሎት ዘርፉን ችግር እየፈታ መሆኑን ጠቁመው÷ ለትውልድ የሚቀመጥ ዳታ በየቀኑ የሚሰበሰብ የአገልግሎት ዘርፉን የሚያዘመን የዳታ ምንጭ ሆኗል ብለዋል።

አንዱ ተቋም ከሌላው ተቋም ጋር መረጃ መለዋወጥ አንዳለበት ጠቅሰው÷ በዚህም በርካታ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በወንድማገኝ ጸጋዬ