የሀገር ውስጥ ዜና

ከንቲባ አዳነች 44 የመኖሪያ ቤቶችና ሱቆች ያሉትን ባለአምስት ወለል ህንጻ ለተጠቃሚዎች አስተላለፉ

By Adimasu Aragawu

May 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ 44 የመኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች ያሉትን ባለአምስት ወለል ህንጻ ለተጠቃሚዎች አስተላልፈዋል።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ዛሬ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ገብስ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ቁጥር 3 የበጎነት መንደር የተገነባውን 44 የመኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች ያሉት ባለአምስት ወለል ህንጻ ለተጠቃሚዎች አስተላልፈናል ብለዋል።

ገብስ ተራ ቀደም ብሎ እጅግ የተጎሳቆለ፣ ለመኖር ምቹ ያልሆነና ባረጁ እና በደቀቁ ቤቶች የተሞላ፣ በተደጋጋሚ በእሳት አደጋ የሚጠቃ፣ ለአቅመ ደካማ እናቶች የማብሰያና የመጸዳጃ አገልግሎት አስቸጋሪ የነበረበት መንደር መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህ መንደር የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 377 የመኖሪያ ቤቶች ያላቸው 5 ህንጻዎች መገንባት መቻሉን የገለጹት ከንቲባዋ÷ ነዋሪዎቻችንም ከዛ አስከፊ አኗኗር ተላቀው ክብራቸውን በሚመጥን ፅዱ፣ ዘመናዊ አኗኗር የሚፈጥር፣ ልጆች ቦርቀው የሚጫወቱበት እና ደረጃውን በጠበቀ መኖሪያ መንደር እንዲኖሩ በማድረጋችን በጣም ደስ ብሎናል ነው ያሉት።

ይህንን የበጎነት መንደር ግንባታ ላይ በክትትል እና ድጋፍ አስተዋጽኦ ያደረጉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን ከምንም በላይ ልበ ቀና ባለሃብቶች በገንዘባቸው ላደረጉት ድጋፍ በነዋሪዎቹ ምስጋና አቅርበዋል።