የሀገር ውስጥ ዜና

በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው ድርሻ …

By Yonas Getnet

May 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር እና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው አለ በኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት።

የጋራ ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደትን አስመልክቶ 14ኛውን መደበኛ ጉባኤ አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በዚህ ወቅት እስካሁን ያለው የምርጫ ሂደት ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር እና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የገለጸው ምክር ቤቱ÷ ይህንን ሚና በተደራጀ መልኩ ለመወጣት እንዲቻል በክልል፣ በዞኖችና በወረዳዎች ደረጃ መዋቅሩን ዘርግቶ በንቃት እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጧል።

የክልሉ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ለፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስራዎች መሳካትና ለዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት አስፈላጊውን በጀት፣ ቢሮ፣ ሎጂስቲክስና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን እያሟሉ እንደሆነ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

ፓርቲዎቹ በምርጫ ሂደት ላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ በከፍተኛ ተነሳሽነትና በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ያለምንም ተፅዕኖ ዕጩዎቻቸውን በማስመዝገብና አባላትን በማደራጀት እኩልና ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረውላቸው የየራሳቸውን የምርጫ ቅስቀሳና አማራጭ ሃሳብ ለሕዝብ እያቀረቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢና የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ አቶ ሞገስ ኢደኤ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች በፉክክርም ሆነ በትብብር ውስጥ ሆነው ሂደቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ እየሰሩ መሆናውን ተናግረዋል።