አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፀረ-ተህዋስያን መድሐኒቶች በጀርሞች መለመድ ችግር ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው አለ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት።
በኢንስቲትዩቱ የአቅም ግንባታ ላቦራቶሪ ዳይሬክተር ዳንኤል መለሰ እንዳሉት÷ በዓለም ላይ ከሚከሰተው ሞት መካከል 9 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው የመድሐኒቶች በጀርሞች መለመድ ችግር ነው።
ችግሩ በኢትዮጵያም በየዓመቱ ከ21 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት እንደሚዳርግ ገልጸው፤ በዚህም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን በየደረጃው በሚገኙ ሆስፒታሎች ለማስፋፋት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ላቦራቶሪ መሰረት ያላደረገ የመድኃኒት አሰጣጥ ለችግሩ መባባስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
በዚህም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በክልሎች የላቦራቶሪ አቅም ግንባታና ማስፋፋት ሥራዎች መከናወናቸውንም ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት።
የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በበኩላቸው፤ መድሐኒቶችን የተላመዱ ፀረ-ተህዋስያን ሰውን ለከፍተኛ ህመምና ሞት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረጉት በመሆኑ ትኩረት ይሻል ብለዋል።
መድሐኒቶችን የተላመዱ ጀርሞች የሚያስከትሉትን ችግር መቀልበስ የሚቻለው የላቦራቶሪ ስርዓቱን እንደ ሀገር ብሎም እንደክልል በማሻሻልና በማጠናከር እንደሆነም አስረድተዋል።
በዮናስ ጌትነት