ቢዝነስ

የባንክ ሒሳብን ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር የማስተሳሰሩ ሒደት …

By Melaku Gedif

May 21, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሁን ላይ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ43 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ደርሷል አለ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተመረጡ ከተሞች ላይ የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች እስከ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ከደንበኞች የፋይዳ መታወቂያ ጋር እንዲተሳሰር ቀነ ገደብ አስቀምጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚህም መሰረት ዜጎች የባንክ ሒሳብ ቁጥራቸውን ቀነ ገደቡ ሳይጠናቀቅ ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር እንዲያስተሳስሩ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ በርካታ ዜጎች የባንክና የቴሌብር ሒሳብ ቁጥራቸውን ቀነ ገደቡ ሳይጠናቀቅ ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር ያላስተሳሰሩ መሆኑን ፋና ዲጂታል ከየባንኮቹ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የባንክ ሒሳብን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የማስተሳሰሪያ ቀነ ገደቡ መጠናቀቁን ተከትሎም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት ደንበኞች ያልተጣመሩ የባንክ ሒሳቦችን ማንቀሳቀስ እንዳይችሉ ተደርጓል፡፡

ያልተሳሰረ የባንክ ሒሳብ እንዳይንቀሳቀስ በመታገዱም ደንበኞች ወደ ባንኮች በመሄድ የማስተሳሰር ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

ባንኮችም የደንበኞችን ጥያቄ ከግምት በማስገባት እንደአሰራራቸው ሁኔታ የደንበኞችን የባንክ ሒሳብ ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር የባንክ ሒሳባቸውን እንዲያንቀሳቅሱ እያደረጉ መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

ስለሆነም ዜጎች የባንክና የቴሌብር ሒሳብ ቁጥራቸውን በፍጥነት ወደ ባንኮች በመሄድ ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር ማስተሳሰር እንዳለባቸው ፕሮግራሙ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ዜጎች የባንክ ሒሳባቸውን ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር የማያስተሳሰሩ ከሆነም የባንክ ሒሳባቸው ከወጪ ግብይት ታግዶ የሚቆይ መሆኑን ነው ያረጋገጠው፡፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በተለይም በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ማጭበርበርን ከመከላከል ባለፈ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር ከፍተኛ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ሒደት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን÷ ዜጎች ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ መሠረት የሆነውን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እንዲያከናወኑ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በሌላ በኩል ደንበኞች የባንክ ሒሳባቸውን ከፋይዳ መታወቂያቸው ጋር እንዲያጣምሩ የተጀመረውን ሥራ አንዳንድ አጭበርባሪዎች እንደአጋጣሚ ለመጠቀም እየሞከሩ በመሆኑ ዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠይቋል፡፡

ባሉበት ሆነው ደንበኛ የሆኑበትን ባንክ ሊንክ ብቻ በመጠቀም ያጣምሩ፤ የሁሉም ባንኮች ማጣመሪያ ሊንክ https://id.et/connect

በመላኩ ገድፍ