የሀገር ውስጥ ዜና

 የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በስፋት ተሰርቷል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

May 21, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በስፋት ተሰርቷል አሉ።

በክክሉ ስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ በ430 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ የባለ ብዙ መንደር የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት÷ የቤተሰብ እና የማህበረሰብ ብልጽግና ማረጋገጥ የመንግሥት ዋነኛ አጀንዳ ነው።

መንግሥት በተለያየ ጊዜ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የህዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል።

60 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገውና 42 የውኃ ቦኖዎች ያሉት ይህ ፕሮጀክት፣ ለአጎራባች ወረዳዎች የሚሆኑ 3 ቦኖዎችንም ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል።

በክልል ደረጃ በዚህ ዓመት 78 የውኃ ፕሮጀክቶች የሚመረቁ ሲሆን፤ በዚሁ ሳምንት 80 ሺህ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርገው የሾኔ የውኃ ፕሮጀክትም ይመረቃል ተብሏል።

በሊያ ዱጉማ