የሀገር ውስጥ ዜና

ምርጫው አካታች እንዲሆን የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል – ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

By Mikias Ayele

May 21, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታች እንዲሆን የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል አሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፡፡

ቦርዱ ለምርጫው በተቋቋሙ ልዩ ምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮች በምርጫው ዕለት ድምጽ ስለሚሰጡበት አግባብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ወታደራዊ ካምፖች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም እንዲሁም ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በድረገጽ አማካኝነት የመራጮች ምዝገባ ማከናወኑ ይታወቃል፡፡

ሰብሳቢዋ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፥ ቦርዱ በተጠቀሱት አካባቢዎች የድምፅ መስጠት ሂደት በምን አግባብ እንደሚከናወን ከፍተኛ ጥናትና ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ተፈናቃዮች በየካምፖቻቸው እንዲሁም በድረ ገጽ የተመዘገቡ ተማሪዎች ወደ አካባቢዎቻቸው ሄደው ድምጽ እንዲሰጡ አስፈላጊው የሎጂስቲክስ ዝግጅት ተጠናቋል ነው ያሉት፡፡

በድረገጽ አማራጭ በተከናወነው የተማሪዎች ምዝገባ ተማሪ ያልሆኑ ሰዎች እንዳይመዘገቡ የማረጋገጥ ሥራ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡

ወታደሮች ከወታደራዊ ደኅንነትና ተፈጥሯዊ ባህሪ አንጻር ድምጻቸውን ባሉበት ካምፕ እንደሚሰጡ መናገራቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡