አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አርሰናል በስፔናዊው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ እየተመራ የ2025/26 የውድድር ዓመት የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወቃል፡፡
ባለፉት ሦስት የውድድር ዓመታት በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አርሰናል በዚህ ዓመት ሻምፒዮን በመሆን ከዚህ ቀደም ራሱ ፅፎት የነበረውን ታሪክ መድገም ችሏል፡፡
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በ2022/23 እና በ2023/24 ማንቼስተር ሲቲን እንዲሁም አምና ሊቨርፑልን በመከተል በሁለተኛነት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ቀደም አርሰናል በአሰልጣኝ አርሰን ቬንገር እየተመራ ለተከታታይ ሦስት የውድድር ዓመት 2ኛ ሆኖ ከጨረሰ በኋላ በአራተኛው የሊጉ ሻምፒዮን ሆኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከ1998/99 እስከ 2000/01 የውድድር ዓመት ድረስ ማንቼስተር ዩናይትድ ለተከታታይ ሦስት የውድድር ዓመት የሊጉ ሻምፒዮን ሲሆን አርሰናል 2ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አይዘነጋም፡፡
በወቅቱ ለተከታታይ ሦስት የውድድር ዓመታት 2ኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀ በኋላ በአራተኛው የውድድር ዓመት (በ2001/02) የሊጉ ሻምፒዮን መሆን ችሏል፡፡
በወቅቱ አርሰናል ካደረጋቸው 38 ጨዋታዎች በ26ቱ አሸንፎ፣ 9 ጊዜ አቻ የተለያየ ሲሆን 3 ሽንፈት አስተናግዶ 87 ነጥብ በመሰብሰብ ነበር ሻምፒዮን የሆነው፡፡
መድፈኞቹ በስፔናዊው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ እየተመሩ በዚህ ዓመት ያሳኩት የሊጉ ክብር በቀድሞው አሰልጣኛቸው አርሰን ቬንገር እየተመሩ ካሳኩት የሊጉ ዋንጫ ጋር አስገራሚ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ፈጥሯል፡፡
አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከመድፈኞቹ ጋር ዋንጫውን ማሳካት ባይችሉም የቀደሙት ዘመናት ታላቅነቱን በማይመጥን ሁኔታ ከዋንጫ ፉክክር ርቆ የቆየውን ክለብ ወደ ተፎካካሪነት በመመለስ ትልቅ ሥራ ሰርተዋል፡፡
በዚህ የውድድር ዓመት አንድ ጨዋታ እየቀረው ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው አርሰናል ካደረጋቸው 37 ጨዋታዎች 25 ድል፣ 7 አቻ እና 5 ሽንፈት አስመዝግቧል፡፡
ሻምፒዮኑ አርሰናል የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነ በ2001/02 የውድድር ዓመት የሊጉ ሻምፒዮን ሲሆን ካሸነፈው 26 ጨዋታ ጋር በተመሳሳይ 26ኛ የሊግ ጨዋታ ድሉ ይሆናል፡፡
አርቴታ አርሰናልን ሲረከብ ቡድኑ ከሊጉ ዋንጫ መራቅ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ መድረክ የሚያሳትፈውን ቦታ ይዞ ለማጠናቀቅ የሚቸገር ቡድን ነበር፡፡
በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የቡድን ግንባታ ሒደት ከ22 ዓመታት በኋላ ከሊጉ ዋንጫ ጋር የተገናኙት መድፈኞቹ የፊታችን እሁድ ዋንጫውን በክብር ይቀበላሉ፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ