የሀገር ውስጥ ዜና

ፌደራል ፖሊስ ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ አቅሙን አሳድጓል – ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

By Adimasu Aragawu

May 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዓለም የደረሰበት የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ አቅሙን አሳድጓል አሉ የተቋሙ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፡፡

117ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ ቀን በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እየተከበረ ነው።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የሀገር ድንበር ተከብሮ ዜጎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ፖሊስ ትልቁን ሚና እየተወጣ ነው።

ተቋሙ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከልና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ከአፍሪካ ብቁና አስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።

በወንጀል መከላከል እና ተያያዥ ፖሊሳዊ ትግበራዎች የዲጂታል ሥርዓቶችን ወደ ሥራ በማስገባት ፖሊሳዊ ሥራዎችን ማዘመን መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የሳይበር ወንጀሎችን፣ የፋይናንስ ማጭበርበሮችን እና የተወሳሰቡ የዲጂታል አሻራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመተንተንና በማስረጃነት በማቅረብ ተቋሙ በአፍሪካ ውስጥ ግንባር ቀደም የቴክኖሎጂ ባለቤት ሆኗልም ነው ያሉት፡፡

ጥቂት ያደጉ ሀገራት የታጠቁትን ትጥቅ በመታጠቅ ከዘመኑ ጋር እኩል እየተራመደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ተቋሙ በቴክኖሎጂ የታገዘ የወንጀል መከላከል አቅም ማሳደጉን ጠቅሰው÷ የትኛውንም የፀጥታ ስጋት ለመቀልበስ የሚያስችለው ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የዲጂታል ማዘዣ ማዕከል፣ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ፣ የድሮን ኃይል እና ዲጂታል ኮሙኒኬሽን ወደ ትግበራ ከገቡ ቴክኖሎጂዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በወንጀል ምርመራ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች እና ሽብርተኝነትን መከላከልን ጨምሮ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ረገድ ውጤታማ ሥራ መከናወናቸውንም አመልክተዋል።

በወንድሙ አዱኛ