አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተደረጉ ዝግጅቶች በተለይም የዲጂታል አማራጮች ጥቅም ላይ መዋላቸው የወጣቶችን ተሳትፎ አሳድጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አሰግደው ኃ/ጊዮርጊስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በምርጫው ላይ ወጣቶች በንቃት መሳተፋቸው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣቶች የምርጫውን ካርድ ከማውጣት ጀምሮ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማሕበር ዋና ጸሐፊ ኤርሚያስ ወንድሙ በበኩሉ ከዚህ ቀደም ወጣቶች ካርድ ለመውሰድ በአካል መገኘት ይጠበቅባቸው እንደነበረ አንስተው÷ ዘንድሮ ግን ይህ አሰራር በመቀየር ምርጫ ቦርድ ባመቻቸው አሰራር ሁሉም ወጣቱ ባለበት ሆኖ መመዝገብ መቻሉን ጠቁሟል።
ቴክኖሎጂ ሁሉም ሰው ዴሞክራሲን ባህል እንዲያደርግና መብቱን እንዲጠቀም ምቹ ዕድል እንደፈጠረም ተናግሯል።
የከተማዋ ወጣቶች ማሕበር ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት ተከስተ አያሌው ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚዲያ የሚያደርጉት የቅስቀሳ ሂደት ውስን መሆኑን አንስቷል።
አሁን ላይ ወጣቶች ለምርጫ በቀላሉ መመዝገብ የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋቱ ትልቅ ለውጥ መሆኑን በመግለጽ÷ በርካታ ወጣቶች ለመምረጥ መመዝገባቸውንና ወጣቱም የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ልምምድ ለማጎልበት ያለውን ከፍተኛ ሚናና ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ አመልክቷል።
በፊት የፓርቲዎች ቅስቀሳ በቴሌቪዥንና በተወሰኑ አማራጮች ብቻ ይተላለፍ እንደነበርና የዘንድሮ ግን በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በቀላሉ መገኘት በምርጫው ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ እንዳደረጋት የተናገረችው ደግሞ ወጣት መልካም በንቲ ናት።
ወጣቷ ካርድ ከማውጣት ጀምሮ ያሉ ሂደቶች በእነዚህ ማሕበራዊ ሚዲያዎች መተላለፋቸው በጣም የተሻለና ትልቅ ለውጥ የመጣበት እንደሆነም አስረድታለች።
በዮናስ ጌትነት