አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ መሃል ፒያሳ የተገነባው የዓድዋ የገበያ ማዕከልና የትራንስፖርት ተርሚናል በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ፒያሳ በቀድሞ አጠራሩ “ዶሮ ማነቂያ” አካባቢን አፍርሰን መልሰን አልምተን፣ አዘምነን አስውበናል ብለዋል።
በዚህም ከ101 በላይ የመሸጫ ሱቆች፣ ከመሬት በታች ሁለት ደረጃ ፓርኪንግ፣ የታክሲ እና የአውቶቡስ ተርሚናል፣ ካፌ እና ሬስቶራንት፣ የመኪና የኤሌክትሪክ ቻርጅ አገልግሎት መስጫ እንዲሁም ፕላዛና ፋውንቴን እንዳለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም 2 ዘመናዊ ሊፍት፣ ቢሮዎች፣ ክሊኒክ እና ፋርማሲ፣ ዘመናዊ የእሳት አደጋ መከላከያ መሳሪያዎች፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ ተገጥመውለት ሱቆቹና ካፍቴሪያዎቹ ለአካባቢው ተነሺዎች በእጣ መተላለፋቸውን አመልክተዋል።
ዛሬ ፒያሳ የጋራ ታሪካችንን “የዓድዋ ድል መታሰቢያን” የገነባንበትና የሀገራት መሪዎች ለጀግኖች ሰማእቶቻችን የአበባ ጉንጉን የሚያኖሩበትን ጨምሮ በርካታ የጋራ መገልገያ እና የቱሪስት ስበትን የጨመሩ መሰረተ ልማቶች የሰራንበት ታሪካዊ ቦታ ሆኗል ነው ያሉት።
ፒያሳ አካባቢ የኮሪደር ልማት የጀመርንበት ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ የዓድዋ የገበያ ማዕከልና የትራንስፖርት ተርሚናል በመጨናነቅ፣ ግፊያ፣ እንግልት፣ በፀሐይ፣ በዝናብ እና አቧራ ላይ ሲንገላታ ለነበረዉ ህዝባችን ንፁህ፣ ምቹ እና ስርዓት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ እንዲሆን አድርገነዋል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜና የጥራት ደረጃ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።