የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የሚወስን ቁልፍ ጉዳይ ነው – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

By abel neway

May 23, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት የሀገርን ኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የሚወስን ቁልፍ የብሔራዊ ጥቅምና የሕልውና ጉዳይ ነው አሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)።

ጥያቄው ታሪካዊነትን ከመልክዓ-ምድራዊነት፣ ሕጋዊነትን ደግሞ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያሰናሰለ ጠንካራና ምክንያታዊ መሠረት ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያና የቀይ ባሕር ዳርቻ ትስስር በሀገረ መንግሥት ምሥረታና ግንባታ ታሪክ ውስጥ እጅግ የጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

ለአብነትም በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን የነበረው ኃያልነትና በአዱሊስ ወደብ አማካኝነት ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች ጋር የተደረገው ሰፊ የንግድ ልውውጥ ከቀይ ባሕር ቁርኝት የመነጨ እንደነበር አብራርተዋል።

በታሪክ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ለማራቅ የውስጥ ባንዳዎችን በማሰለፍ ጭምር የሸረቡት ሴራና የተሳሳተ ስሌት በእጅጉ የሚያስቆጭ የታሪክ ስብራት መሆኑን ጠቁመዋል።

ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለማደናቀፍ የውጭ ኃይሎችና የእነርሱ ተላላኪ የሆኑ የሀገር ውስጥ ኃይሎች በተሳሳተ ስሌት እየተጓዙ መሆኑን አክለዋል።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የባሕር በር ጉዳይን ማንሳት እንደ ተንኳሽነት የሚቆጠርበትን አደገኛ ትርክት በመስበር፣ ወሳኝ የምክክርና የንግግር አውድ እንዲፈጠር መደረጉን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ይፋ ካደርጉበት ጊዜ ጀምሮም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሥራዎች ማከናወኑን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ላይ የተደመረ ዕይታና ፅኑ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።በምንም ዓይነት የፖለቲካ ልዩነት የትውልድን ጥያቄ አሳልፎ መስጠት እንደማይገባና ለብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት መከበር በትብብር መቆም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን በሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ እያቀረበች መሆኑን በመጥቀስ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ቦሊቪያና ፔሩ፣ ብራዚልና ፓራጓይ፤ በአፍሪካ የማሊ፣ ሴኔጋልና ኮትዲቯር የተጠቀሙባቸውን የጋራ መፍትሔዎች በተሞክሮነት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 መሠረት የኢኮኖሚ ውህደት የሰፈነባት አህጉር ለመፍጠር በቀጣናው ሀገሮች መካከል የኃይል ትስስር በመፍጠር የባሕር በር ፍላጎቷን በሰፊው እያስረዳች መሆኑንም ገልጸዋል።

የባሕር በር አለመኖር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በየዓመቱም ኢትዮጵያ ለወደብና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ብቻ ከአንድ ነጥብ አምስት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለማድረግ መገደዷን ተናግረዋል።

ይህም በወጪና ገቢ ንግድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲሁም በጠቅላላው የዕድገት ጉዞ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስገንዝበዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ መግባባትን በማጉላት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ማስረዳት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን በማስከበር ዕድገትና ብልፅግና ከሚወስኑ ቁልፍ ብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል።