ስፓርት

በሺያመን ዳይመንድ ሊግ አትሌት አዲሱ ይሁኔ አሸነፈ

By abel neway

May 23, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2026 የዳይመንድ ሊግ ሁለተኛ መዳረሻ በሆነችው የቻይናዋ ሺያመን ከተማ በወንዶች 5 ሺህ ሜትር አዲሱ ይሁኔ አሸንፏል።

አትሌት አዲሱ 12፡57.32 በሆነ ሰዓት ውድድሩን ያጠናቀቀ ሲሆን ይህም የዓመቱ የዓለማችን ፈጣኑ ሰዓት እንዲሁም የውድድሩ አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊው አትሌት ቢኒያም መሐሪ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቅቋል፡፡ በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር በለፈው ሳምንት በሻንግሀይ ዳይመንድ ሊግ ያሸነፈችው አትሌት ብርቄ ሀየሎም በዛሬው ዕለት 2ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።

አትሌት ሳሮን በርሄ 6ኛ እና አትሌት ወርቅነሽ መሰለ 15ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቀዋል፡፡

በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር የተሳተፉት አትሌት ኬና ቱፋ 5ኛ፣ አትሌት ዓለምናት ዋለ 8ኛ እና አትሌት ፍሬሕይወት ገሰሰ 9ኛ ሆነው ውድድሩን ጨርሰዋል።