አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እና እስላማዊ እሴቱን በመጠበበቅ ሊያከብር ይገባል አለ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ የ1 ሺህ 447ኛውን የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የጠቅላይ ምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሸይኽ አብዱልከሪም ሸይኽ በድረዲን÷ የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በመረዳዳት እና በመተጋገዝ ሊያከብረው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ የልማት እና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሀሚድ ሙሳ በበኩላቸው÷ በዓሉ የነቢዩሏህ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ታማኝነት፣ መስዋዕትነትና ትዕግስት የሚታወስበት በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ መንፈሳዊ እሴቱን ጠብቆ ሊያከብረው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዓሉን አቅመ ደካሞችን፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትንና ህሙማንን በመጠየቅና በመርዳት እንዲሁም ለሀገር ሰላም እና ለህዝቦች አንድነት በመስራት ማክበር ይገባል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ሙስሊሙ ማህረሰብ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፍና ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የተለመደ በጎ ሚናውን እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል።