አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ቀን የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) በፈረንጆቹ 1963 መመስረቱን አስመልክቶ የሚከበር በዓል ነው።
አፍሪካውያን የድንቅ መልከዓ ምድራዊ ተፈጥሮ፣ የቀደምት ስልጣኔ እና የታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት እንዲሁም ብዙ ሺህ ዘመን የቆየ የባህል፣ ቋንቋ፣ የሀይማኖት ባለቤት ቢሆኑም በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች በደረሰባቸው ወረራ ምክንያት ለዘመናት አንድነትን አጥተው ቆይተዋል፡፡
በተለይም አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በተካሄደው የበርሊን ጉባኤ ያሳለፉት የቅኝ ግዛት ውጥን ሀሳብ ለአፍሪካውያን ጥቁር ታሪክ መነሻ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከ1885 እስከ 1960ዎቹ ከሀገራችን ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ በስተቀር ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር የወደቁ ሲሆን፤ ዘመናትን ለዘለቀ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል፡፡
አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካ ወረራ በፈጸሙበት ወቅትም የመሬት መንጠቅና የጉልበት ብዝበዛ፣ ግድያ እና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እንዲሁም የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶችን ወደ አውሮፓ በማጓጓዝ የዝርፊያ ተግባር መፈፀማቸውን ታሪክ ያስረዳል፡፡
ይሁን እንጂ በ1888 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተጋድሎ የተገኘው ድል የአፍሪካ ሀገራት ለፀረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ እንዲነሳሱ በር ከፍቷል።
ይህንን ድል ተከትሎ ትግሉ ተቀጣጥሎ መላ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ ባደረጉት ትግል በ1960ዎቹ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ መሆን ችለዋል፡፡
ከፀረ-ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ማግስት አፍሪካውያንን በአንድ ድርጅት በማሰባሰብ በአፍሪካዊ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ ለማድረግ ከብዙ የሀሳብ ክፍፍሎች እና ልዩነቶች በኋላ በፈረንጆቹ 1963 የአፍሪካ አንድንት ድርጅት ተመሰረተ፡፡
ድርጅቱ እንዲመሰረት ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥታለች፤ የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤትም በአዲስ አበባ ተተክሏል።
ድርጅቱ ከተመሰረተ በኋላ ባሉት ዓመታት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ለውጦችን ተከትሎ ራሱን ያደሰ ሲሆን በፈረንጆቹ 2002 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በይፋ ተሰርዞ በአወቃቀሩ እና በዓላማው የተሻሻለው የአፍሪካ ህብረት ተወልዷል።
ድርጅቱ የተመሰረተበትን እለት ተከትሎም 63ኛው የአፍሪካ ቀን በአፍሪካ ህብረት አዘጋጅነት በተለያዩ መርሐ ግብሮች በመከበር ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀኑን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በአፍሪካ አህጉራዊ አንድነት እና ተጨባጭ እድገት እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአፍሪካ ትልቁ ሀብቷ ህዝቦቿ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ አንደ አንድ ነፃ ሉዓላዊ እና ኩሩ ሀገር ከማንኛውም የአፍሪካ ሀገር ጋር በአንድነት መንፈስ ትቆማለች ብለዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ