ቢዝነስ

ወደ ቻይና የሚላኩ ምርቶች የወጪ ንግድ ፍቃድ በሁሉም ባንኮች እንዲሰጥ ተወሰነ

By Hailemaryam Tegegn

May 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ቻይና የሚላኩ ምርቶች የወጪ ንግድ ፍቃድ በሁሉም ባንኮች እንዲሰጥ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በሁለቱ ሀገራት አጠቃላይ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ትብብር ስምምነት መሠረት ወደ ቻይና የሚላኩ ምርቶች የወጪ ንግድ ፍቃድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ እንዲሰጥ ተወስኖ እንደነበር ባንኩ አስታውሷል፡፡

ነገር ግን የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ዘርፍ ይበልጥ ለማቀላጠፍ፣ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና ለላኪዎች ምቹና ተደራሽ የባንክ አገልግሎት ለመፍጠር ቀደም ሲል የነበረው ገደብ ሙሉ በሙሉ መነሳቱን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቻይና የሚላኩ ማንኛውም አይነት የወጪ ንግድ ምርቶች የፍቃድ አሰጣጥ ሰነድ ማደራጀትና ተያያዥ የባንክ አገልግሎቶች በሀገሪቱ ውስጥ ፍቃድ ባላቸው በሁሉም ባንኮች በኩል መስተናገድ ይችላሉ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሁሉም የንግድ ባንኮች ከተለመዱት የወጪ ንግድና የውጭ ምንዛሪ መመሪያዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለደንበኞቻቸው አገልግሎቱን እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡