የሀገር ውስጥ ዜና

ስልጣን በምርጫ የሚገኝ እንጂ እንደ ቅርጫ የሚከፋፈል አይደለም – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Hailemaryam Tegegn

May 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ስልጣን በምርጫ የሚገኝ እንጂ በጉልበት ወይም እንደ ቅርጫ የሚከፋፈል አይደለም አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባዋ በዛሬው ዕለት በመዲናዋ የተካሄደውን የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የምናፀናበትና የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ሕዝቡ መሆኑን የምናስመሰክርበት ነው ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ ያለበት በሕዝብ ይሁንታ ብቻ ነው የሚል ጽኑ እምነት እንዳለው ገልጸው፥ አንዱና ዋናው ግባችን ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ማድረግ ነው ብለዋል።

በእስካሁኑ ጉዞ ብልፅግና ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ስልጣን የሚመነጨው በሕዝብ ይሁንታ መሆኑን በማመን ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ እያራመዱ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን የፓርቲዎችን ሀሳብ በክርክርና በሌሎች መንገዶች ለህዝብ እንዲደርስ በማድረግ ፅኑ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት ሀሳባችንን ለሕዝባችን አድርሰናል ያሉት ከንቲባዋ፥ ሕዝቡ ጥሩ ዳኛ እንደሆነ በማመን በፅናት ውሳኔውን እንጠብቅ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡