የሀገር ውስጥ ዜና

የብልጽግና ፓርቲ በድሬዳዋ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሄደ

By Mikias Ayele

May 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልጽግና ፓርቲ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የምረጡኝ ቅስቀሳ እና የማጠቃለያ የድጋፍ ሰልፍ አካሂዷል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በወቅቱ እንዳሉት÷ ፓርቲው ችግሮችን በፅናት በማለፍ “ትናንትን ማከም፤ ዛሬን መግጠም፤ ነገን መተለም” በሚል መርህ እየሠራ ይገኛል።

በኢኮኖሚው ዘርፍ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ማጠናቀቅ መቻሉን፣ ሀገሪቱን ከስንዴ አስመጪነት ወደ ላኪነት ማሸጋገሩን እና በኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ መቀየር መቻሉን ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲን መምረጥ የሀገሪቱን ክብር ከፍ ለማድረግ፣ የባሕር በር ፍላጎትን ለማረጋገጥ እና ጠንካራ የሕገ መንግሥት ሥርዓት ለመገንባት ያስችላል ያሉት ከንቲባው፤ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ድምፃቸውን ለፓርቲው እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው÷ በለውጡ ዓመታት በማኅበራዊ ልማት፣ በትምህርት ቤት ምገባ፣ በከተማና በኮሪደር ልማት እንዲሁም ዲፕሎማሲን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ፓርቲው የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ነዋሪዎች የብልጽግና ፓርቲን እንዲመርጡ ጠይቀዋል።

በተሾመ ኃይሉ