አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል፡፡
ትብብሩ በምረጡኝ ቅስቀሳው ለዜጎች የተሻለ ሐሳብ ይዞ መምጣቱን በመግለጽ ሕዝቡ እንዲመርጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፕሬዚዳንት አብርሃም ጌጡ በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያውያን የምርጫ ካርዳቸውን በመጠቀም ለሀገር ይጠቅማል የሚሉትን ፓርቲ እንዲመርጡ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሻለ ሐሳብ ይዞ መቅረቡን በማንሳት መራጮች ትብብሩን እንዲመርጡ ጠይቀዋል።
የትብብሩ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት መጋቤ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት በበኩላቸው÷ ዜጎች በምርጫው በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የጠንካሮች ስብስብ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ÷ ኢትዮጵያን በሚወክል አደረጃጀት መዋቀሩንም ገልጸዋል፡፡
ትብብሩ አሁን ያለው ጊዜ ሰላማዊ ትግልን የሚፈልግ መሆኑን በመጠቅስ÷ ይህንን ሰላማዊ ትግል ሊያደናቅፉ የሚችሉ ብዙ እንቅፋቶች ቢኖሩም ችግሮችን በመጋፈጥ ምርጫ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ጋር በመሆን ሰላማዊ ትግል በማድረግ ለኢትዮጵያ የተሻለ የልማት እና የእድገት እድልን ለማምጣት መስራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሚልኪያስ አዱኛ