የሀገር ውስጥ ዜና

ሆስፒታሉ ኢትዮጵያ ራሷን ለመቻል ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

May 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የላፍቶ ሆስፒታል ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ራሷን ለመቻልና ለሀገራዊ ልማት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገነባው የላፍቶ ሆስፒታል በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ሆስፒታሉ በጤናው ዘርፍ የረቀቁ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ግንባታ ለማስቀጠል አሻጋሪ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

በተሻሻለው የመከላከልና አክሞ የማዳን የጤና ፖሊሲ መሠረት ኢትዮጵያን ቀዳሚ የህክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለተሰነቀው ርዕይ መሰል ተቋማትን መገንባት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በ5 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ግዙፍ ሆስፒታል እጅግ ዘመናዊ አቅሞችን በመጠቀም ለካንሰር፣ ውስብስብ ለሆነ የልብ ህመምና ተያያዥ የህክምና ሁኔታዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ህክምና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ሆስፒታሉ ዜጎች እዚሁ ሀገራቸው ውስጥ ልዩ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን፥ ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ይህ ታላቅ ተቋም የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ከመቀየር ባለፈ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ራሷን ለመቻልና ለሀገራዊ ልማት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው ብለዋል።