አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዘመኑ የደረሰባቸውን የላቁ የህክምና ቴክኖሎጂዎች ያካተተ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገነባው የላፍቶ ሆስፒታል በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሆስፒታሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ተገንብቷል፡፡
የካንሰር እና የልብ ሕክምናዎችን በላቀ ደረጃ በመስጠት ዜጎች ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያስቀርና የሀገርን የውጭ ምንዛሪ የሚያድን ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚደገፉ በዓለም ላይ ያሉ የመጨረሻ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያካተተ መሆኑ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
በ5 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ሆስፒታሉ 17 ዘመናዊ ህንጻዎችን ያቀፈና 500 አልጋዎችን የመያዝ አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሕብረተሰቡ የተሻለና ዘመናዊ ሕክምና ተደራሽ ለማድረግ ታልሞ መገንባቱን ጠቅሰው፥ ግንባታው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡